ኢንሼቲቩ ሚሊዮኖችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ቢሮው አስታወቀ

በናይል ተፋሰስ አገራት የሚከናወኑት በርካታ ፕሮጀክቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ አስታወቀ፡፡

የናይል ተፋሰስ በተፋሰሱ አካባቢ ለሚገኙ ማህበረሰቦች የጋራ ተፈጥሮአዊ ሀብት መሆኑን ኢንሼቲቩ ገልፆ አባል አገራቱ ውሃውን በፍትሃዊነት በማልማት ተጠቃሚ ለመሆን እንቅፋት የሚሆኑ ጉዳዮችን ለመቀነስና ለመከላከል በትኩረት መስራት አለባቸው ብሏል፡፡   

የምስራቅ አፍሪካ የናይል ተፋሰስ አገራት የቴክኒክ ቢሮ ዋና ዳይሬክተር አቶ ፈቅ አህመድ ከዋልታ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት የናይል ተፋሰስ አገራት የህዝባቸውን የላቀ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ፖለቲካልና ቴክኒካል ትብብራቸውን ማጠናከር አለባቸው፡፡

የናይል ተፋሰስ ኢንሼቲቭ የጋራ ራዕይና አጋዥ የተሰኙ ሁለት የስትራቴጂክ የድርጊት መርሀ ግብር መንደፉን ዋና ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

አቶ ፈቅ እንዳሉት የጋራ ራዕይ መርሀ ግብር የአገራትን አቅም ማጎልበት ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ የአቅም ግንባታ ሥራው በተፋሰሱ አገራቱ መካከል ጠንካራ ግንኙነትን ለመፍጠር ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡

መልካም ተሞክሮዎችን ለመለዋወጥ፣አመኔታን ለመፍጠርና ለቀጣናው ትብብር አቅም ለመፍጠርም ይረዳል፡፡

አጋዥ መርሀ ግብሩ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ፣ሱዳንና ግብፅ ዜጎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚተገበር መሆኑን አቶ ፈቅ ተናግረዋል፡፡ ኢንሼቲቩ በተለይም በድንበር ተሸጋሪ ኢንቨስትመንት ባስተዋወቃቸው በርካታ ፕሮጀክቶች ሶስቱ አገራት ተጠቃሚ መሆናቸውን ነው ያስረዱት፡፡

የተፋሰስ ልማት፣ የኃይል አቅርቦትና መስኖ ልማትን ጨምሮ ስምንት ያህል ግዙፍ ፕሮጀክቶች በአገራቱ ተግባራዊ መደረጋቸውን ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡

በኢትዮጵያ በጣና በለስ 86ሺ ሄክታር መሬት ፣ በሱዳን አትባራ ደግሞ 64ሺ ሄክታር  መሬት ላይ የተፋሰስ ልማት የተከናወነ ሲሆን የናስር ሀይቅን ከደለል ሙሌት ለመከላከል ከ500 ኪሎ ሜትር በሚበልጥ መሬት ላይ ግብፅ የተፋሰስ ሥራ ሰርታለች፡፡  

ፕሮጀክቱ የአገራቱን ህዝቦች ተጠቃሚነት ከማሻሻልና አካባቢውን ከመራቆት መታደግ በተጨማሪ የተፋሰስ ልማት አስተዳደር ሥርዓት ለማጠናከር  እንደሚረዳ አቶ ፈቅ ገልፀዋል፡፡

የምስራቅ አፍሪካ የተፋሰስ ልማት አንድ ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን 110 ሚሊዮን ሰዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ከኢንሼቲቩ የተገኙት መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡  

ከኢትዮጵያ ወደ ሱዳን የሚዘረጋው የኤሌክትክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር በሶስቱ አገራት መካከል የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭን በቀላሉ ለማከናወን ይረዳል፡፡ የአገራቱን ግንኙነትን ለማጠናከርም ሚናው የጎላ ነው፡፡

አገራቱ ሶስት ሺ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ሽያጭ ያከናውናሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ የኃይል ሽያጩን የምታከናውነው ኢትዮጵያ ለሱዳን አንድ ሺ 200 ሜጋ ዋት፣ለግብፅ ደግሞ ሁለት ሺ ሜጋ ዋት ልትሸጥ ትችላለች፡፡

ዘርፈ ብዙ የጋራ ፕሮግራሙ የሶስቱን አገራት የድንበር ተሸጋሪ ኢንቨስትመንት በማጎልበት በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና አካባቢን በዘላቂነት ከመራቆት ለመከላከል እንደሚረዳ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

አካባቢያዊ ቅንጅትን ለማጠናከርና ብሔራዊ አቅምን ለማጎልበት የሚረዱ ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም አቶ ፈቅ ገልፀዋል፡፡ በትንበያ፣በድንገተኛ አደጋ፣በማስጠንቀቂያ፣በዝግጁነትና የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ተገቢውን ምላሽ በመስጠት ዙሪያ በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡