ሚድሮክ ለረጅም ጊዜ ከልሎ ባቆያቸው ቦታዎች ላይ ግንባታ ጀመረ

ሚድሮክ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች በይዞታነት ይዟቸው ለረጅም ጊዜ ከልሎ ባቆያቸው ቦታዎች ላይ ግንባታ ጀመረ፡፡

ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤትና ከመዲናዋ አስተዳደር የተዋቀረ ኮሚቴ ግንባታቸው የተጀመሩና ያልተጀመሩ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ፕሮጀክቶችን ጎብኝቷል።

ሚድሮክ በዋናነት በፒያሳ፣ በሜክሲኮ አደባባይ እና ቦሌ የሚገኙ ፕሮጀክቶቹን ግንባታ በይፋ አስጀምሯል፡፡

ኩባንያው ፒያሳ አካባቢ ከ16 አመት በፊት በተረከበው ቦታ ላይ በፍጥነት ወደ ስራ ያልገባው አካባቢው አለታማና ለግንባታ አስቸጋሪ በመሆኑ እንዲሁም የህንፃ ዲዛይን በተደጋጋሚ እንዲቀያየር በማስገደዱ መሆኑን የኩባንያው የግንባታ ፕሮጀክቶች ዋና ስራ አስፈፃሚ ኢንጂነር ባሲም አልዳሂር ተናግረዋል፡፡

ቀደም ሲል ከ40 እስከ 50 ፎቅ ለመገንባት በቅድሚያ እቅድ ቢያዝም በአካባቢው አስቸጋሪነት የተነሳ ከፍታው ወደ አራት ወለል ዘመናዊ የገበያ ማእከል ዲዛይን መቀየሩን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚው ያስረዱት፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ኩባንያው ከሰባት ዓመታት በፊት ከተረከባቸው አካባቢዎች መካከል በቦሌ አራት ህንፃዎችን ለመገንባት ተንቀሳቅሶ ሁለቱን ሙሉ በሙሉ ሲያጠናቅቅ፤ የሁለቱ የቁፋሮና መሰረት የማውጣት ስራ እየተከናነባቸው ናቸው፡፡

በሜክሲኮ አካባቢ ባለ37 ፎቅ ለመስራት የታቀደው ፕሮጀክት በተለያዩ ውስጣዊ ችግሮች ግንባታው መቋረጡን የሚድሮክ ኢትዮጵያ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት ገብረመስቀል  ገልፀዋል፡፡ ይህ ቦታ ከስድስት ዓመት በላይ ታጥሮ መቆየቱም ነው የተነገረው፡፡

በካሳንቺዝ አካባቢ ባለ15 ፎቅ ለመገንባት ከአምስትና ስድስት ዓመት በፊት መሰረት ወጥቶለት ግንባታው የተቋረጠ ፕሮጀክት መኖሩም ተጠቅሷል፡፡

ኩባንያው ከ10 ቢሊዮን ብር በላይ ፈሰስ የሚያደርግበት የሸራተን አዲስ ማስፋፊያ በቀጣይ ወደስራ የሚገባ ትልቅ ፕሮጀክት ነው ተብሏል፡፡

የማስፋፊያ ፕሮጀክቱ በ31 ሄክታር መሬት ላይ የሚርፍ ሲሆን መንደሮች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ አረንጓዴ የመዝናኛ ስፍራዎችን ያካትታል፡፡

የፖሊስ ጋራዥ ከአካባቢው በፍጥነት ባለመነሳቱ የግንባታው ጊዜ እጅግ እንዲዘገይ እንዳደረገው ዋና ሥራ አስፈፃሚው አስታውሰዋል፡፡

ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ወደስራ ላለማስገባት ኩባንያው የነበሩበት ችግሮች በጥሩ ደረጃ  በመፈታታቸው ግንባታዎቹ በፍጥነት ይከናወናሉ ብለዋል- አቶ አብነት ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው በበኩላቸው ኩባንያው የያዛቸው ፕሮጀክቶች በታሰበው ፍጥነት ወደስራ ቢገቡ ለከተማዋም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ዕድገት የላቀ ሚና እንደሚኖራቸው ተናግረዋል፡፡

‹‹የፕሮጀክቶቹ ግንባታ መፋጠን ይኖርበታል›› ያሉት አቶ አባተ መንግስት የግንባታ ክትትልና ቁጥጥር ስራውን ከመቼውም ጊዜ በላቀ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

የሚድሮክንና የሌሎችን ፕሮጀክቶች ተፈፃሚነት ለመከታተል ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት እና ከከተማ አስተዳደሩ የተውጣጣ ቡድን መሰየሙንም ምክትል ከንቲባው አስታውሰዋል፡፡

ኩባንያው በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ አጠቃላይ ወጪያቸው ከ24 ቢሊዮን ብር በላይ የሆኑ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ወደ ሥራ ማስገባቱ ተመልክቷል፡፡

ሚድሮክ ኮንስትራክሽን አፍሪካ ህብረት ዋና ፅህፈት ቤት አጠገብ የሚገነባውን እጅግ ዘመናዊ ሆቴል ጨምሮ ናኒ ህንፃ፣ ሰላም ሆስፒታል፣ ሳራ ኮምፕሌክስን የገነባና በመገንባት ላይ የሚገኝ ግዙፍ ኩባንያ ነው፡፡