ሚኒስቴሩ ኢትዮጵያ ከእንፋሎት ኃይል 5ሺ ሜጋዋት ለማመንጨት ማቀዷን አስታወቀ

ኢትዮጵያ ከእንፋሎት ኃይል 5ሺ ሜጋ ዋት እስከ 2029 ዓመተ ምህረት ድረስ ለማመንጨት ማቀዷን የማዕድን፣ ነዳጅና ተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስትሩ አቶ ሞቱማ መቃሳ 6ኛውን የምስራቅ የአፍሪካ የስምጥ ሸለቆ እንፋሎት ጉባዔ መክፈቻ ላይ እንደገለጹት ፤ኢትዮጵያ ከታዳሽ የተፈጥሮ ሐብት ኃይል የማመንጨትን ተግባርና  ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር በትብብር ለመስራት እያደረገችው ያለውን ጥረት ይበልጥ አጠናክራ ትቀጥላለች ፡፡

ሚንስትሩ ኢትዮጵያ 22 የእንፋሎት ኃይል ማመንጫ ቦታዎችን እንደተለዩና የአሉቶና የተንዳሆ የእንፋሎት ኃይል ማመንጫዎች ሥራ መጀመራቸው አስታውቋል ፡፡

በዚህም መሰረት የአሉቶ 70 ሜጋ ዋት እንዲሁም የተንዳሆ 100 ሜጋ ዋት የማመንጨት አቅም እንደሚኖራቸውም ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ በመሰረተ ልማት ትስስር፣ በግንባታና በፖሊሲ ማማከር እንዲሁም በሌሎች የሁለትሽ ግንኙነት ሥራዎች ከሌሎች የአፍርካ አገሮች ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር ፍላጎት እንዳላትም  አመልክቷል፡፡

በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይልና የገንዘብ አቅም ውስኑነት አፍሪካን በኃይል ግንባታና ልማት ሥራዎች ላይ ውጤታማ እዳትሆን እንቅፋት እንደሆኑባትም ነው ከመድረኩ የተገለጸው ፡፡

ኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ልማትን በ2003 ዓመተ ምህረት ከነበረው አሁን ላይ በአምስት እጥፍ ማሳደግ መቻሏን ነው የተገለጸው፡፡

ሀገሪቷ ከውሃ ማመንጫዎች 45 ሺ ሜጋ ዋት፣ ከንፋስ 1ሺ350 ሜጋ ዋት ከእንፋሎት ኃይል 7ሺ ሜጋ ዋት እንዲሁም ከጸሐይ በቀን 5 ኪሎ ዋት የማመንጨት ዓቅም እንዳላት ተነስቷል ፡፡

7ነጥብ5 ቢሊየን ከሚሆነው የዓለማችን ሕዝብ 1ነጥብ1 ቢሊየን ያህሉ ምንም የኤሌክትሪክ አቅርቦት እንደማያገኝ ጥናቶች ያስረዳሉ፡፡

በተመሳይ ሁኔታ ከአፍሪካ ሕዝብ 25 በመቶ የሚሆነው ብቻ ነው የኤሌክትሪክ አገልግሎት የሚያገኘው፡፡

የ6ኛውን የምስራቅ አፍሪካ የስምጥ ሸለቆ እንፋሎት ጉባዔ በተባበሩት መንግስታት የአፍሪካ የኢኮኖሚ ኮሚሽን የጉባዔ ማዕከል እስከ ጥቅምት 27 በአዲስ አበባ ድረስ እንደሚቆይ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘገቧል፡፡

ኤርትራ ይህ ጉባዔ እንደታዘጋጅ ዕድሉ ቢሰጣትም አገሪቷ ካላባት የውስጥና የውጭ ችግር አንፃር ጉባዔውን ማዘጋጀት ባለመቻሏ ኢትዮጵያ ለሁለተኛ ጊዜ ኮንፍረንሱን እንድታዘጋጅ መደረጉንም ለማወቅ ተችሏል ፡፡