ባለስልጣኑ መንግስት የወሰነው የገቢ ግብር ቅነሳ በገቢ መጠን ጫና አለማሳደሩን አስታወቀ ፡፡

መንግስት በገቢና በሰራተኞች ደሞዝ ግብር ላይ የወሰደው የቅነሳ እርምጃ በሚሰበሰበው የገቢ መጠን ላይ ጫና አለማሳደሩን የትግራይ ክልል ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ ፡፡

የባለስልጣኑ የገቢ ዝግጅት ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ሸዊት ሓጎስ ለዋልታ እደገለጹት፤ ዘንድሮ መንግስት በገቢ ግብርና በሰራተኞች ደሞዝ ግብር ያደረገው ቅነሳ በሚያሰባሰቡት ገቢ ላይ የራሱ ጫና ያሳድራል የሚል ስጋት አሳድሮባቸው እንደነበረ ነው፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ ባለፉት ሶስት ወራት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለማሰባሰብ የታቀደው እንኳን ሲታይ ከ936 ሚሊየን ብር በላይ ነው ማግኘት የተቻለው ፡፡

አሁን የተገኘውም ገቢ ራሱ ከዓምናው ሶስት ወር ጋር ሲነጻጸር በነጥብ 55 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ የሚያበረታታ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ይህም በክልሉ በተለይም በደረጃ ሀ ያሉ ግብር ከፋዮች ከሐምሌ 1 እስከ 30 ድረስ የግብር መክፈያ ቀን በሚል ስያሜ ነጋዴው ከመንግስት አካላት ጋር በመተባበር በዘመቻ ያካሄዱት ስራ ውጤታማ መሆኑን አብራርተዋል ፡፡

እንደዚሁም የንግዱ ማህበረሰብ ግብር የመክፈል ግዴታውና ገቢ ለሀገር ግንባታ ያለው ፋይዳ  ግንዛቤው ከጊዜ ወደ ግዜ እያደገ መምጣቱን ያሳያል ነው ያሉት፡፡

በትግራይ ክልል በተያዘው በጀት ዓመት ከ3ነጥብ6 ቢሊየን ብረ በላይ ከተለያዩ የግብር ምንጮች ለማሰባሰብ አቅደው እየሰሩ መሆናቸውን አቶ ሸዊት ጠቁመዋል ፡፡