በህዳሴ ግድብ ዋንጫ ከ1ነጥብ1 ቢሊየን ብር በላይ ተሰበስበ

በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ዋንጫ አስካሁን 1ቢሊየን ብር በላይ መሰብሰቡን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ ገብረእግዚአብሔር ለዋልታ እንደገለጹት፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በአምስት ክልሎች በመዘዋወር ለስራው ማስፈጸሚያ 1 ቢሊየን 158 ሚሊየን ብር ገቢ ተገኝቷል ፡፡

ዋንጫው በተዘዋወረባቸው ከቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል 33 ሚሊየን ብር፣ ከአፋር 71 ሚሊየን ብር፣ ከትግራይ 81 ሚሊየን ብር፣ ከአማራ 432 ሚሊየን ብር እንዲሁም ከኦሮሚያ 541 ሚሊየን ብር ማስገኘት እንደቻለ አብራርተዋል ፡፡

ዋንጫው አሁንን የሚገኘው በኦሮሚያ ክልል እንደሆነም ነው ያመለከቱት ፡፡

አቶ ኃይሉ አያይዘውም በኦሮሚያ ክልል ቀደም ሲል ተፈጥሮ የነበረው አለመረጋጋት በገቢ ማሳባሰባሰቡ ላይ የጎላ ተፅዕኖ እንዳልነበረውና ከታቀደው ገንዘብ በላይ ገቢ እደተገኘ አስረድተዋል፡፡

የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ዋንጫ የኦሮሚያ ክልል ቆይታውን ሲያጠናቅቅ ወደ ደቡብ ሕዝቦች፣ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል እንደሚጓዝ አቶ ኃይሉ አስታውቀዋል፡፡

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ በቦንድ ግዢና ስጦታ አስካሁን 8ነጥብ 9 ቢሊየን ብር መሰብሰቡን ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ገቢ ማሰባሰቢያ 2 ቢሊየን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ እተየሰራ እንደሆነም አንስተዋል፡፡

በዚሁም ታላቁ የህዳሴ ግድብ አንድ የፖለቲካ ኢኮኖሚያዊ ሕብረተሰብ ለመፍጠር የሚደረገውን ጥረት ማገዙን ነው የገለጹት ፡፡

ጽሕፈት ቤቱ  በጊዮን ሆቴል የገቢ ማሰባሰቢያውን ይበልጥ ለማነቃቃት የሚያስችል ውይይት ነገ ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች፣ ማሕበራትና ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ጋር ውይይት እንደሚያደርግ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡