በሩብ ዓመቱ ከቱሪዝም ዘርፍ ከ 872 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ተገኝቷል

ኢትዮጵያ በሩብ ዓመት ከቱሪዝም ዘርፍ ከ872 ሚሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቷን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ አባተ በዛሬው ዕለት ለጋዜጠኞች በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት ባለፉት ሦስት ወራት በአጠቃላይ 233ሺ 32 የሚሆኑ የውጭ ቱሪስቶች አገሪቱን በመጎብኘታቸው 872 ሚሊዮን 471ሺ808 የአሜሪካ ዶላር ገቢ ለማግኘት ተችሏል ።

በዘንድሮ የበጀት ዓመት ሩብ ዓመት የተመዘገበው የጎብኚዎች ቁጥርና ከዘርፉ የተገኘው ገቢ ከዓምናው ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጻር በጥቂቱም ቢሆን መቀነሱን የገለጹት አቶ ገዛኸኝ አባተ ለዚህም በአንዳንድ አገሪቱ አካባቢዎች የተከሰቱ ሁከቶች አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን ተናግረዋል ።

አንዳንድ የውጭ አገራት ጎብኚዎች ወደ አገሪቱ የሚያደርጉትን ጉዞ እንዳይሰርዙ ለማድረግ  የተቋቋመው የቱሪዝም  ኮማንድ ፖስት በአገር ውስጥና በውጭ አገራት የተለያዩ ጥረቶችን እያካሄደ በመሆኑ የቱሪስት ፍሰቱ እያደገ መምጣቱን አስረድተዋል ።

ኮማንድ ፖስቱ አገሪቱን ለመጎብኘት የሚመጡ የውጭ ቱሪስቶች ደህንነታቸው እንዲጠበቅ  ለማስቻልም ከተለያዩ የሚመለከታቸው የባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊ ሁሉ እየተከናወነ እንደሚገኝ በመግለጫው ተመልክቷል ።