የዓለም ባንክ አካል የሆነው የዓለም አቀፉ የገንዘብ ትብብር(IFC) የኢትዮ-ጅቡቲን የነዳጅ መስመር ፕሮጄክት ግንባታ 1ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር እንደሚያግዝ ገለጸ ፡፡
የድርጅቱ ዋና የኢንቨስትመንት ባለሙያ ካሊም ሻህ እንደገለጹት ፤ በደቡብ አፍሪካ የሚገኘውና ብላክ ሪኖ ተብሎ የሚጠራው የመሰረተ ልትና ኢንቨስትመንት ቡድን ከጅቡቲ ወደ ኢትዮጵያ የሚዘረጋውን የ550 ኪሎ ሜትር የነዳጅ መስመርን በገንዘብ ለመደገፍ ለኢትዮጵያ መንግስት ያረበው ጥያቄ ተቀባይት አግኝቷል ፡፡
የፕሮጄክቱ ጠቅላላ ወጪ 1ነጥብ 55 ቢሊየን ዶላር ሊደርስ እንደሚችልና ግንባታው ተጠናቆ ወደ ተግባር ሲሸጋገር በአንድ ቀን 240 ሺህ በርሜል ነዳጅ ማጓጓዝ እንደሚችል አስታውቀዋል፡፡
መስመሩ የ51 ሴንቲሜትር ስፋት ሲኖረው የ950 ሺህ በርሜል ነዳጅ ማጠራቀም የሚችል ቋት እንደሚኖረውም ነው ያመለከቱት ፡፡
መስመሩ የነጭ ጋዝ፣ ጋዝና የአውሮፕላን ነዳጅ ወደ ኢትዮጵያ ያስተላልፋል ነው የተባለው ፡፡
ፕሮጄክቱን የሚገነባው አካል ለ30 ዓመታት ያህል ካስተዳደረው በኋላ የኢትዮጵያ መንግስት እንደሚረከበውም ተመልክቷል፡
የነዳጅ መስመሩ ኢትዮጵያ ከጅቡቲ ወደ ሀገር ውስጥ በከባድ ነዳጅ ጫኚ ተሸከርካሪዎች ለማጓጓዝ የሚወጣውን ከፍተኛ ገንዘብ፤ ጊዜና ጉልበት እንደሚቀንስና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ የታገዘ እንደሚሆንም አስታውቀዋል ፡፡
በአሜሪካን የኢንቨስትመንት ቡድን የሚደገፈው ድርጅት የአዋጪነት ቅድመ ጥናት እንዳደረገና ወደ ተግባር ሲሸጋገር የመጀመሪያው የነዳጅ መስመር እንደሚሆን ነው ያመለከተው ፡፡
የኢትዮጵያ የነዳጅ ፍላጎት በ10 በመቶ እንደዳደገና አሁን ላይ ዓመታዊ የነዳጅ ፍጆታዋ 3ነጥብ6 ሜትሪክ ቶን ደርሷል ነው የተባለው ፡፡
የኢትዮጵያ ለነዳጅ በየዓመቱ 2ነጥብ8 ቢሊየን ዶላር ወጪ እንደምታደርግ ከአፍሪካ ኮሙኒቲ ማህበረሰብ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የኢትዮጵያና ጅቡቲ መንግስታት በነዳጅ መስመሩን ግንባታ በተመለከተ በ2007 ስምምነት ላይ መድረሳቸው ይታወሳል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የጅቡቲ-አዋሽ የነዳጅ መስመር በፋይናንስ ከመደገፍ ባሻገር የኢትዮጵያን የጨርቃጨርቅ፣ ቆዳና ሲሚንቶ ኢንዱስትሪዎችንም ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ገልጸዋል፡፡
ጉዳዩን በሁለቱ መንግስታት ተቀባይነት ካገኘና የስምምነት ፊርማ ከተቀመጠ በኋላ ወደ ተግባር ለመሸጋገር የሚያስችሉ ተግባራትንና ጥናቶችም እንደቀጠሉ ባለሙያው አስረድተዋል ሲል ዋልታ ዘግቧል ፡
ትርጉም ሰለሞን ዓይንሸት