የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅመም የገበያ አማራጮችን ማስፋት ወሳኝ መሆኑ ተገለጸ

በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚቀርቡ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ምርቶች  የገበያ አማራጮችን ማሳደግ ምርቶቹ ተገቢውን ዋጋ እንዲያገኙ በማስቻል ለዘርፉ ዕድገት ወሳኝ ሚና የሚጫወት መሆኑን የንግድ ሚኒሰትር ዲኤታ አቶ አሰድ ዚያድ ገለጹ ።        

6ኛው የጥራጥሬ ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ዓለም አቀፍ ጉባኤ በዛሬው ዕለት በኢንተር ኮንቲኔንታል ሆቴል በተከፈተበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት አቶ አሰድ ዚያድ እንደገለጹት ለጥራጥሬ፣ ለቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ምርቶች የተሻለ የገበያ ትስስር መፍጠርና የገበያ ዕድሎችን መፍጠር ለዘርፉ እድገት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ተናግረዋል ።        

አሁን ወቅቱ የሦስቱን ምርቶች የገበያ አማራጮች የማስፋፊያ፣ የገበያ ትስስሩንና ስብጥሩን ለማጠናከር  አዳዲስ የገበያ ዕድሎችን የማፈላለጊያወቅት መሆኑን የጠቆሙት  አቶ ዚያድ   የዘርፉን ዋነኛ የንግድ አካላትን በማስተባባር   ምርቶቹ ላይ እሴትን በመጨመር ዘርፉን ይበልጥ እንዲመነደግ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

እንደዚህ አይነት ጉባኤዎች መካሄዳቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓለም አቀፍ ገበያ ዋጋቸው እየወረደ የመጣውን የጥራጥሬ ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማቅመም ምርቶች ላይ መፍትሄ  የሚያፈላለግ  ስትራቴጂን በመንደፍ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው አቶ አሰድ አስረድተዋል ።           

ኢትዮጵያ በጥራጥሬ ፣ በቅባት አህሎችና በቅመማቅመም ምርት ያልተነካና ለኢንቨስትመንት የሚጋብዝ  እምቅ ሃብትና  ምቹ የአየር ፀባይ ባለቤትም መሆኗን አቶ አሰድ አያይዘው ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ የምርት ገበያ የኢንተርኔት ቀጥታ የግብይት ሥርዓትን  በመዘርጋት  የጥራጥሬ ፤ የቅባት እህሎችና የቅመማቅመም  ምርቶችን የግብይት ሥርዓት ዘመናዊ በማድረግ በኩል ኢትዮጵያ በአፍሪካ ተምሳሌት በመሆን ላይ እንደትምኝም አቶ አሰድ ተናግረዋል ።     

በአገሪቷ  ከጥራጥሬ፣ ከቅባት እህሎችና ከቅመማቅመም ምርቶች የምታገኘው ገቢ ከዕቅዱ በታች መሆኑን የሚናገሩት አቶ አሰድ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን  በዘርፉ ምርታማነትን በማሳደግና ጥቅም ላይ የሚውለውን የመሬት መጠን  በማሳደግ  በዕቅድ ዘመኑ የተያዘውን ግብ  ለማሳካት ጥረት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል ።   

የዓለም ጥራጥሬ ኮንፈዴሬሽን ፕሬዚደንት ሚስተር ሁሴን አርስላን በበኩላቸው  የታዳጊ አገራት  በመጠን ከፍ  ያለ የጥራጥሬ ምርትን፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅምም ምርቶችን በማምረት  የምግብ ዋስትናን  ከማረጋገጥ ጀምሮ ከዘርፉ የሚያገኙትን ገቢ ማሳደግ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል ።

በተጨማሪም ታዳጊ አገራት በምርት ወቅት የሚያጋጥመውን ብክነት ለመቀነስ ትኩረት ሠጥተው  መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው  ሚስተር ሁሴን አመልክተዋል ።  

የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት አህሎችና ቅመማቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚደንት አቶ ኃይሌ በርሄ በበኩላቸው እየተካሄደ ያለው ጉባኤ በዘርፉ የንግድ አማራጮችን ለማስፋትና  የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ  የዘርፉ  ተዋናዮች መካከል  የንግድ ግንኙነቶች እንዲጠናጠር ይረዳል ብለዋል ።   

በዛሬው ዕለት በተጀመረው ጉባኤ  በአጠቃላይ  210  ተሳታፊዎች የተገኙ ሲሆን  103  የሚሆኑት በዓለም አቀፍ ደረጃ የተለያዩ ኩባንያዎችንና አገራት  ወክለው የመጡ መሆናቸውን አቶ ኃይሌ አስታውቀዋል ።

6ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማቅመም ጉባኤ  “ የግብርና ምርቶች  ግብይት  ቀጣይነት ላለው  ዓለም አቀፍ ንግድ” በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።