ኢትዮጵያ ለኢኮኖሚያዊ ዕድገት ወሳኝ የሆነውን የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማጠናከርና ለማሳፋፋት የምታደርገው ጥረት በአፍሪካ በተምሳሌትነት እየተጠቀሰ ነው፡፡
የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት 50ኛ ዓመት ትናንት በኢንተርኮኒቲኔንታል ሆቴል ሲከበር እንደተገለፀው ኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊ ሽግግርን ለማፋጠን ለኢንዱስትሪ ዘርፍ የሰጠቸው ትኩረት ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በአርዓያነት የሚጠቀስና የሚበረታታ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁና ብዙ ኩባንያዎችን ማስተናገድ የሚችሉ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ዘርፉን ለማሳደግ እየሰራች እንደሆነም ተመልክቷል፡፡
የውጭ ባለሀብቶችን ከመሳብ በተጓዳኝ የአገር ውስጥ ባለሀብቶች ዘርፉን እንዲቀላቀሉ ተገቢውን ድጋፍና ምቹ ሁኔታዎችን የመፍጠር ሥራም እየሰራች መሆኗ ተጠቁሟል፡፡
የኢንዱስትሪ ሚነስትር ዴኤታ አቶ አለሙ ስሜ መንግስት ለኢንዱስትሪ ልማት ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመንቀሳቀሱ የተለያዩ አገራት የፋይናንስ ድጋፍ ፍላጎት እያሳዩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በኦሮሚያ፣አማራ ትግራይና ደቡብ ብሔሮች፣ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ለሚገነቡት አራት የተቀናጀ አግሮ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ለመገንባት በሚደረገው ጥረትም የገንዘብ ድጋፍ እየተገኘ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለእነዚህ ፓርኮች የደቡብ ኮሪያ ኤግዚም ባንክ ግማሽ ቢሊዮን ዶላር ለመስጠት መስማማቱን ለማሳያነት ጠቁመዋል፡፡ መጠኑ ባይገለፅም የጣልያን መንግስትም ፍላጎት ማሳየቱን ገልፀዋል፡፡
በፌዴራል መንግስት ለሚተዳደሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ የዓለም ባንክም የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎት ማሳየቱን አቶ ዓለሙ ተናግረዋል፡፡
የአገራቱ ፍላጎት ኢትዮጵያ የኢንዱስትሪ ዘርፍን ለማሳደግ የጀመረችው ጥረትና እየሄደችበት ያለው ጎዳና አዋጭና ተመራጭ የመሆኑ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ለኢትዮጵያ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጉንም ገልፀዋል፡፡
በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዳይሬክተር ሚስተር ዢን ባኮሌ የአፍሪካ አገራት የኢንዱስትሪውን ልማ ለማፋጠን በሚያርጉት ሂደት ድርጅቱ ተገቢውን ድጋፍ እያረገ መሆኑን ተናረዋል፡፡
ላለፉት ሀምሳ ዓመታት የቴክኒኪና ሌሎች ለኢንዱስትሪ ልማት አጋዥ የሆኑ የቁሳቁስ ድጋፎችን ሲያከናውን መቆየቱን ጠቁመዋል፡፡ የኢትዮጵያን ጥረት ያደነቁት ዳይሬክተሩ አፍሪካውያን የኢንዱስትሪ ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረትና በቁርጠኝነት መንቀሳቀስ አለባቸው ብለዋል፡፡