የኢትዮጵያን የልማት ራዕይ ለማሳካት በአገልግሎት፣ ምርትና በሌሎችም ዘርፎች ጥራትን መሠረት በማድረግ መሥራት የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጉዳይ መሆኑን የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ዶክተር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያ ጥራትና ሽልማት ድርጅት የበላይ ጠባቂ ሆነው በተመረጡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር ባለሃብቶች የጥራትን ጽንሰ ሐሳብን ከድርጅቶቻቸው ህልውና ጋር ማያያዝ እንደሚገባቸው ገልጸው፤ የጥራት ድርጅቱ የግብርናውን ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሸጋገር ካለው ጉልህ ድርሻ አንጻር በቀጣይም እንደ አንድ ባለድርሻ መታየት እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡
በዘመነ ግሎባላይዜሽን የገበያ ተወዳዳሪነትን አስፈላጊነት በአግባቡ በመረዳትና ተወዳድሮም በአሸናፊነት ለመወጣት ይቻል ዘንድ ባለሃብቶች ምርቶቻቸውንና አገልግሎቶቻቸውን ባልተጋነነ ዋጋ ማቅረብ እንዳለባቸውም ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል፡፡
የጥራት ድርጅት ቀደም ሲል አራት ሀገራዊ የጥራት ሽልማቶችን አወዳድሮ የሸለመና በዚህም ውጤት ያስገኙ ባለሃብቶችና ድርጅቶች ስኬታቸው ለሀገራዊ ህዳሴ መረጋገጥ የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ አረጋግጠዋል፡፡
ባለሃብቶች ለአገሪቱ ዕድገትና ብልጽግና እያበረከቱት ያለው አስተዋፅኦ ጥራትን መነሻና መድረሻ ያደረገ እንዲሆን ከማድረግ አኳያ የሚጠበቅባቸውን ሀገራዊ ኃላፊነት በመወጣት ራሳቸውንና አገራቸውን እንዲያሳድጉ ለማድረግ መንግስት አስፈላጊ ሁኔታዎችን ያመቻቻል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንትና የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ ዶክተር አድማሱ ፀጋዬ በመክፈቻ ንግግራቸው ድርጅቱ ካለው ጉልህ ሀገራዊ አስተዋጽኦ አንጻር በአነስተኛ በጀት እየተንቀሳቀሰ መሆኑ ቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት አቅሙን እንዲያጎለብት የባለድርሻ አካላት ድጋፍ እንደሚያስፈልገው ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ እስካሁን አራት ሀገራዊ ሽልማቶችን አወዳድሮ የሸለመ ሲሆን አምስተኛው ውድድር ዝግጅት እየተካሄደ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
ውድድሩ በተለይ አምራቾች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶች ዘመናዊ አሰራር እንዲላበሱ፣ ጠንካራ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ፣ የደንበኛን እርካታ በማጎናጸፍና የለውጥ ማሻሻያዎችን በማድረግ ድርጅቶቻቸው ውጤታማ እያደረገ መሆኑን ዶክተር አድማሱ አክለው ገልጸዋል፡፡
በዕለቱ የኢትዮጵያ ጥራትና ሽልማት ድርጅት የመተዳደሪያ ደንብ ይፋ ተደረጓል፤ ለቀደምት የቦርድ ዳኞች ጉባዔና የቴክኒክ ኮሚቴ አባል ለነበሩ የምስጋና የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ የጥራትና ሽልማት ድርጅት በጥር 2001 ዓ.ም. በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከልና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መመሥረቱ ይታወሳል፡፡