የሐዋሳ -ጩኮ መንገድ ግንባታ ለሌላ የሥራ ተቋራጭ ተሠጠ

ከሦስት ዓመት  በፊት  ግንባታው  ተጀምሮ  በሚጠበቀው  ሁኔታና  የጊዜ ገደብ ሊጠናቀቅ ያልቻለው  የሐዋሳ- ጩኮ የ66 ኪሎሜትር  የመንገድ ግንባታ ለሌላ የሥራ ተቋራጭ መሠጠቱን  የኢትዮጵያ መንገዶች  ባለሥልጣን አስታወቀ ።

በባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ለዋልታ እንደገለጹት የትራንስ አፍሪካ  ሃይዌይ መንገድ አካል የሆነው የ66 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው የሐዋሳ-ጩኮ መንገድ  958 ነጥብ 9  ሚሊዮን ብር  በላይ በሆነ ወጪ በህንዱ ኤስ ኢደብሊው በተባለ   ኩባንያ ግንባታው ሲከናወን ቆይቷል ።

ሆኖም ኩባንያው የመንገዱን ግንባታ ለማጠናቀቅ ሦስት ዓመት የተሠጠው ቢሆንም  በተሠጠው የጊዜ ሰሌዳ 33ነጥብ 8 በመቶ ብቻ  በማጠናቀቁና የግንባታው ጥራት ባለመጠበቁ ከተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች  በኋላ ባለሥልጣኑ ከኩባንያው ጋር  የነበረውን ውል መሰረዙን አቶ ሳምሶን አስረድተዋል።   

እንደ አቶ ሳምሶን ማብራሪያ ባለሥልጣኑ  የሐዋሳ -ጩኮ መንገድ ፕሮጀክትን ለማከናወን ጥሩ አፈጻጻም ያላቸውን ሰባት የሥራ ተቋራጮች በጨረታ በማወዳደር ለሲኖ  ሃይድሮ  ኮርፖሬሽን ለተባለ የቻይና  ኩባንያ  በሁለት ዓመት  ገንብቶ እንዲያስረክብ የሠጠ ሲሆን  ለግንባታው በአጠቃላይ  965 ሚሊዮን  247ሺ ብር ተመድቧል ።

የሐዋሳ-ጨኮ የመንገድ ግንባታ በሦስት ኮንትራት ተከፋፍሎ ግንባታው የሚከናወነው የሐዋሳ-አገረማሪያም የ198 ኪሎሜትር መንገድ አካል ሲሆን ግንባታው  ሙሉ ሙሉ ሲጠናቀቅ አዲስ አበባን ከኬንያ ሞምባሳ ወደብ ጋር በቀጥታ ያገናኛል ተብሎ ይጠበቃል ።

የሐዋሳ -ጩኮ  መንገድ  ፕሮጀክት ሙሉ  ወጪ   የሚሸፈነው   በአፍሪካ  ልማት ባንክና  በኢትዮጵያ  መንግሥት  መሆኑን  ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።