ባለፉት አራት ዓመታት 3ነጥብ 21ሚሊዮን ህዝብ ከፀሃይ ኃይል ተጠቃሚ ሆኗል

ባለፉት አራት ዓመታት በተለይ የኤሌክትሪክ ኃይል በሌለባቸው የአገሪቱ የገጠር አካባቢዎች 3ነጥብ 21 ሚሊዮን የሚሆን የህብረተሰብ ክፍል ከፀሃይ የኃይል ምንጭ  ተጠቃሚ  መሆኑን የውሃ ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ብዙነህ ቶልቻ ለዋልታ እንደገለጹት ከ2005 ዓም ጀምሮ በአገሪቱ ተግባራዊ በተደረጉት የተለያዩ የፀሃይ ኃይል ፕሮጀክቶች 3ነጥብ 21 ሚሊዮን ህዝብ ተጠቃሚ ሆኗል ።

ከዓለም ባንክ በተገኘ አጠቃላይ የ357 ሚሊዮን ብር ድጋፍ በአራት ዓመታት ውስጥ ከ40ሺ በላይ የሶላር ቁሳቁሶች ተሠራጭተው 210 ሺ የሚሆኑ በተለያዩ ክልሎች የገጠር አካባቢዎች የሚገኙ ነዋሪዎችን የፀሃይ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል ።

እንደ አቶ ብዙነህ  ገለጻ በተጨማሪም  ከዓለም ባንክ ድጋፍ  ከዋናው  የኤሌክትሪክ ማሠራጫ መስመር ርቀት ባላቸው የአገሪቱ  አካባቢዎች ለሚገኙ  545  የጤና ኬላዎችና  370 የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች  የፀሃይ ኃይል መሣሪያዎች የተተከሉ ሲሆን  3 ሚሊዮን የሚደርስ ህዝብን  ተጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል ።

በአሁኑ ወቅት ታዳጊ ክልሎች በሆኑት በአፋር ፣ በሶማሌ፣ ቢኒሻንጉልናጋምቤላ ክልሎች ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ፕሮጀክትን ተግባራዊ ለማድረግ ሥራዎችን እያካሄዱ  መሆኑን የጠቆሙት አቶ ብዙነህ ከተለያዩ ድጋፍ ጪዎች በተገኘ 30 ሚሊዮን ብር  የፀሃይ ማሾዎች እየተከፋፈለና የፀሃይ ማመንጫ መሣሪያዎች ተከላ እየተከናወነ መሆኑን  አስረድተዋል ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በአጠቃላይ 1 ሚሊዮን ሰዎችን በፀሃይ ኃይል ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለማድረግ የሚያስችል ፕሮጀክትን በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለማድረግ ከተባበሩት  መንግሥታት የልማት ድርጅት ( ዩኤንዲፒ) የ73 ነጥብ 1ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር ድጋፍ ማግኘቱን አቶ ብዙነህ አመልክተዋል ።

በፕሮጀክቱም 220ሺ በላይ የፀሃይ ኃይል መሣሪያዎች ተሠራጭተው ጥቅም ላይ ይውላሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ ብዙነህ አያይዘው ገልጸዋል ።

ኢትዮጵያ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ከፀሃይ ኃይል 300 ሜጋ ዋት ለማመንጨት ዕቅድ ያላት ሲሆን በመታህራ፣ በሁመራ እና መቀሌ እያንዳንዳቸው 100 ሜጋዋት ማመንጨት የሚያስችሉ ፕሮጀክቶችን ለማካሄድ ጨረታ አወጥታለች ።