የኢትዮጵያ የግብርና ምርምር ስራዎች ከዓለም ገበያ ሁኔታ ጋር የተገናዘቡ እንዲሆኑ እንደሚደረግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት እና ሴክሬቴሪያት ከተቋቋመ በኋላ የመጀመሪያ ጉባዔውን ዛሬ አካሂዷል።
በጉባዔው ላይ የምክር ቤቱ ስራ የግብርና ምርምሩ በሀገራዊ የልማት ፖሊሲ እና ስትራቴጂ ላይ ተመርኩዞ የሚካሄዱትን የምርምር ስራዎች አቅጣጫ የሚያሲዝ፣ የሚደግፍ እና የሚያስተሳስር መሆኑ ተመልክቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች በዓይነት፣ በጥራት እና በመጠን ተወዳዳሪ ሆና በዓለም የግብርና ኢኮኖሚ ውስጥ ትልቅ ሚና እንዲኖራት የሚያስችል የምርምር ስራ ይከናወናል ብለዋል።
የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለዓለም ገበያ በመጠንና በጥራት ተወዳዳሪ ሆና የውጭ ምንዛሬ ግኝቷን የምታሳድግበት አቅጣጫም ይዘረጋል ነው ያሉት።
ምክር ቤቱም አርሶ አደሮች ገበያ ተኮር ምርቶች ላይ እንዲያተኩሩ ማስቻል፣ በእንስሳት ዘርፍ ያለውን የምርምር ስራዎች ማጠናከር እና ልዩ ድጋፍ በሚሹ ክልሎች ሁለንተናዊ የግብርና ምርምር ስራዎች ያከናውናል ብለዋል።
የግብርናው ዘርፍ እያደገ ሲሄድ በመጠኑ ግዙፍ ሊሆን የሚችለው ባዮማስ በአስተማማኝ ሁኔታ ለባዮ ኢንደስትሪው ግብዓት እንዲሆን የማስቻል ስራ እንደሚከናወንም አብራርተዋል።
ከግብርናው ዘርፍ አንፃር ሀገሪቷ ተጠቃሚ እየሆነች ባለመሆኑ በምክር ቤቱ አማካኝነት ሀገራዊ የግብርና ምርምር ብቃትን የማጎልበት ስራዎች በስፋት እንደሚከናወኑም ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም የግብርናው ዘርፍ ወደ ኢንደስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ዋነኛ ሞተር በመሆኑ ምክር ቤቱ የግብርና ልማቱን ለማገዝ ወቅታዊ እና አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን እንዲሁም እውቀቶችን ያቀርባል ብለዋል።
ምክር ቤቱ ለጋራ ሀገራዊ የልማት ግብ ስኬትም የምርምር አቅምና ብቃትን ማሳደግ እና አዋጭ ቴክኖሎጂዎችን ለተጠቃሚዎች የማብቃት ስራም እንደሚያከናውን ገልፀዋል።
የምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶክተር ካሱ ይላላ በበኩላቸው፥ የግብርና ምርምር ስርአቱ የምግብ ዋስትና በአስተማማኝ ለማረጋገጥና የግብርና ምርቶችን ተጠቃሚነት ለማስፋት የተለያዩ ስራዎች እያከናወነ ነው ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱም ስራዎቹን በተጠናከረ መንገድ ለማስቀጠልና የተያዘውን ግብ ለማሳካት በከፍተኛ ሃላፊነት እንደሚሰራአቶ ካሱ ይላላ ተናግረዋል።
ከትናንት ጀምሮ ለ3 ቀናት በአዲስ አበባ የሚካሄደው ጉባዔ በእፅዋት ዝርያ፣ የዘር ጥራት ቁጥጥርና ኳራንታይን አሰራር ስርዓትን ጨምሮ በሌሎች የግብርና ምርምር ስራዎች ላይ ይመክራል።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ምክር ቤት እና ሴክሬቴሪያት በ2008 ዓ.ም መቋቋሙ ይታወሳል።(ኢዜአ)