ባለሥልጣኑ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የኮንትራት ስምምነት ፈጸመ

የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን ከ2 ቢሊዮን  ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገዶችን ደረጃ ለማሳደግና ለመገንባት የሚያስችሉ  አራት የኮንትራት  ስምምነቶችን ፈጸመ ።

የኢትዮጵያ  መንገዶች ባለሥልጣን የአራቱንም  የመንገድ ፕሮጀክት የኮንትራት ስምምነቱን የተፈራረመው ከተለያዩ አራት ኩባንያዎች ጋር ሲሆን ባለሥልጣኑን በመወከል የኮንትራት ስምምነቱን የፈጸሙት ዋና ዳይሬክተሩ አቶ አርአያ ግርማይ ናቸው ።

ከባለሥልጣኑ  ጋር  የመንገድ  ግንባታ  ኮንትራት ስምምነትን የፈረሙት ሰናን ኮንስትራክሽን ኩባንያን በወከል ዋና ሥራ አስኪያጁ አቶ በቃህኸ ኝ መኮንን ፣ የቻይና ሬል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕን በኩል  ሊቹ አን ፣ የንኮማንድ ኮንስትራክሽንን  በመወከል አቶ የምሩ ነጋና   በድርባ ደፈርሻ ጠቅላላ  የሥራ ተቋራጭን  በመወከል አቶ ድርባ ደፈርሻ  ናቸው።

የመጀመሪያው የመንገድ ፕሮጀክት 76 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው የአበቦ መንገድ በአስፓልት ደረጃ የሚገነባ ነው የተባለው ።

 ግንባታውን ለማከናወን ጨረታ አሸንፎ የውል ስምምነት የፈረመው ቻይና ሬል ዌይ ሰቨንዝ ግሩፕ የተባለ ዓለም አቀፍ የቻይና የሥራ ተቋራጭ ሲሆን  በ960 ሚሊዮን 130ሺ 379 ብር ወጪ በሦስት ዓመት ተኩል አጠናቆ ለማስረከብ ተስማምቷል ።

ሌላው ባለሥልጣኑ በሁለተኛ ደረጃ የኮንትራት ስምምነት የፈረመው በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል የሚገነባው የአሶሳ-ዳለቲ -ባሩዳ የ36 ኪሎሜትር የአስፓልት መንገድ ፕሮጀክት መሆኑን ነው የገገለጸው ።

የባለሥልጣኑ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ እንደገለጹት የአሶሳ-ዳሊቲ-ባሩዳ  የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን  የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበው  227 ሚሊዮን 400 ሺ ብር ውጪ ለማከናወን የኮንትራት ስምምነት የፈጸመው አገር በቀል የሆነው ሰናን ኮንስትራክሽን የተባለ የሥራ ተቋራጭ  ድርጅት ነው ።

የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታው ሲጠናቀቅ የአሶሳ ዞንን በአካባቢው ከሚገኙት ወረዳዎች ጋር  የሚያገናኝ  ነው ብሏል ።

የሳይ-ማጂ  የመንገድ ፕሮጀክት  ባለሥልጣኑ በሦስተኛ ደረጃ የፈረመው ኮንትራት  መሆኑን የገለጹት አቶ ሳምሶን  በደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጠጠር ደረጃ የሚገኘውን በአስፋልት ደረጃ  ለመገንባት ታቅዷል ።

የ29 ኪሎሜትር የሚረዝመውን የሳይ-ማጂ መንገድ ግንባታን ለማከናወን ጨረታ ያሸነፈው ንኮማንድ ኮንስትራክሽን የተባለ አገር በቀል የሥራ ተቋራጭ ድርጅት ሲሆን የግንባታው በጀት 773 ሚሊዮን 77ሺ ብር የኢትዮጵያ መንግሥት መመደበuቡን አስታውቀዋል  ።

የመንገድ ግንባታው ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ አገልግሎት መሥጠት ሲጀምር የሹርማ እና የኩማ ወንዞችን  የሚያገናኝ መሆኑንና  ምርትና ሸቀጦችን ለማጓጓዝ የሚፈጀውን ጊዜና ወጪን የሚቀንስ እንደሆነ አመልክቷል ።

በአራተኛ ደረጃ የኮንትራት ስምምነት የተፈረመበት የደብረ ማርቆስ ከተማ የአስፓልት መንገድ ማስፋፊያ ፕሮጀክት መሆኑን  አቶ ሳምሶን ገልጸዋል ። 

የ4ነጥብ9 ኪሎሜትር እርዝመት ያለው የማስፋፊያ ፕሮጀክቱን ድርባ ደፈርሻ የተባለ አገር በቀል የመንገድ ተቋራጭ በ 212 ሚሊዮን 157 ሺ ብር ግንባታውን  ለማከናወን መስማማቱን አረጋግጧል ።

የመንገድ ግንባታው የኢትዮጵያ መንግሥት በመደበው ገንዘብ የሚከናወን  ሲሆን ግንባታው ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ  የከተማዋን ዕድገት ለማፋጠንና ተጨማሪ ውበት እንደሚሆናት መግለጻቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል