ሳዑዲ ዓረቢያ በግብርናው መስክ ለመሰማራት ያሳየችውን ፍላጎት እንድታሳካ ኢትዮጵያ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሳዑዲ ዓረቢያ የአካባቢ፣ የውኃና የግብርና ሚኒስትር ኢንጂነር አብዱራህማን ቢን አብዱልሙህዚን አልፋድሊ የተመራውን የልዑካን ቡድን ትናንት በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል።
የልዑካን ቡድኑ ከጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ጋር የሳዑዲ ባለሀብቶች በግብርና ዘርፍ በሚሰማሩበት ሁኔታ ዙሪያ መክረዋል።
በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ መላክ በሚቻልበት ስልት ላይም ተወያይተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ በግብርና ምርቶች ላይ ዕሴት ተጨምሮ ወደ ውጭ እንዲላክ ፍላጎት አላት።
መንግስት እሴት የተጨመረባቸው የግብርና ምርቶች ለአገር ውስጥ ገበያ እንዲቀርቡ የገበያ ትስስሩን ለመፍጠር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
ሳዑዲ ዓረቢያ በግብርናው መስክ መሰማራቷ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት እንደሚያጠናክር ጠቁመው፤ ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችልም ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በኢትዮጵያ የግብርና ዘርፍ ለመሰማራት ምቹ ሁኔታዎች እንዳሉም አስረድተዋል።
የሳዑዲ ባለሀብቶች በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ጨምረው ለአገር ውስጥና ለውጪ ገበያ እንዲያቀርቡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ማቅረባቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ዳይሬክተር ጀኔራል አቶ ተመስገን ዑመር ገልጸዋል።
የሳዑዲ ዓረቢያ የአካባቢ፣ የውኃና የግብርና ሚኒስትር ኢንጂነር አብዱራህማን ቢን አብዱልሙህዚን አልፋድሊ በበኩላቸው "ኢትዮጵያ በተለይ በግብርናው መስክ ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ እንዳላት እናምናለን" ብለዋል።
ይህን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ የሚያጠና አንድ ቡድን መቋቋሙንም ጠቁመዋል።
ቡድኑ የዘርፉን ምቹ የኢንቨስትመንት ሁኔታ ካጠና በኋላ የአገራቸው ባለሃብቶች እንደሚሰማሩም አመልክተዋል።
በግብርና ምርቶች ላይ እሴት ጨምሮ ለሁለቱም አገሮች ገበያ የማቅረብ ዕቅድ መኖሩንም ጠቁመዋል።