በአማራ ክልል በ2008/2009 ዓ.ም የመኸር ምርት ዘመን 63 በመቶ የሚሆነው ሰብል መሰብሰቡን የክልሉ ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡
በምርት ዘመኑ በዘር ከተሸፈነው አራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር 116 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ለመሰብሰብ መታቀዱን በቢሮው የሠብል ልማትና ጥበቃ ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ የስራ ሂደት አስተባባሪ ዶክተር ሽመላሽ የሻነህ ለዋልታ ገልፀዋል፡፡
በክልል ደረጃ በተደረገ የዳሰሳ ጥናት ዕቅዱን ለማሳካት እንደሚቻል መገምገሙን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ እስከ ባለፈው ሳምንት ድረስ 63 በመቶ የሚሆነው ሰብል የተሰበሰበ ሲሆን አሁንም ሰብሉን የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ነው የተናገሩት፡፡
በሰሜን ሸዋና በኦሮሞ ብሔረሰብ ዞኖች ከ21 ሚሊዮን በላይ የግሪሳ ወፍ መከሰቱን ጠቁመው ይህም ጉዳት ሳያደርስ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር መዋሉን አስረድተዋል፡፡ አልፎ አልፎ ውርጭ እንደሚያጋጥም ተናግረው ይህም ቢሆን ሰብሉ በመድረሱ ዕቅዱን የማስተጓጎል አቅም እንደሌለው ገልፀዋል፡፡
በምርት ዘመኑ የታየው ዝናብና የአየር ሁኔታ ከዘር እስከ ፍሬ ድረስ ምቹ መሆኑ ‹‹ ዕቅዱን ለማሳካት ያስችላል›› ይላሉ ዶክተር ሽመላሽ፡፡
ቀድሞ የተዘሩ ምርቶችን በመሰብሰብ እርጥበቱ ሳይለቅ በአንድ ማሳ ላይ በዳግም ምርትና በምርት ቅብብሎሽ ስልት ተጨማሪ ምርት የመሰብሰብ ሥራ ጥሩ ውጤት ማስመዝገቡን አስተባባሪው ተናግረዋል፡፡ በዚህም በአንድ የምርት ዘመን ሁለት ጊዜ በማምረት ተጨማሪ ምርት የመሰብሰብ ዕቅድ ከተጠበቀው በላይ ተሳክቷል ብለዋል፡፡
በመሆኑም እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች የሚበቅሉና በፍጥነት የሚደርሱ እንደ ሽምብራ፣ ምስር፣ ጓያ፣ ማሾን የመሳሰሉ ጥራጥሬዎችና የተለያዩ የገብስ ዓይነቶች በመዝራት በዳግም ሰብል ምርት 364ሺ 671 ሄክታር በዘር ለመሸፈን ታቅዶ ከ91 በመቶ በላይ ተሳክቷል፡፡
ከዚህ በተጓዳኝ በሰብል ቅብብሎሽ ስልት ሰብሉ ደርሶ መድረቅ ብቻ በሚጠብቅ 36ሺ 430 ሄክታር መሬት ከላይ የተጠቀሱትን ሰብሎች ለመዝራት ታቅዶ 164 በመቶ አፈፃፀም በማስመዝገብ ከዕቅድ በላይ ማሳካት ተችሏል፡፡