በዘንድሮው የመኸር ወቅት 57 ነጥብ7 በመቶው የሰብል ምርት ተሰብስቧል

በ2008/09 በመኸር ወቅት በሰብል ከተሸፈነው ምርት ውስጥ እስካሁን ድረስ 57ነጥብ 7 በመቶ የሚሆነው የሰብል ምርት  መሰብሰቡን የእርሻና የተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር አስታወቀ ።

በሚኒስቴሩ በሰብል ልማት ዘርፍ የሰብል ልማት ከፍተኛ ባለሙያ የሆኑት አቶ ስዩም ፋለስ ለዋልታ እንደገለጹት በመላ አገሪቱ በመኸር ወቅት  በሰብል  ከተሸፈነው 13 ሚሊዮን 349 ሺ 715 ሄክታር መሬት ውስጥ በ7ሚሊዮን 699ሺ 205 ሄክታር መሬት ላይ የሚገኘው የሰብል ምርት መሰብሰቡን ተናግረዋል ።

የትግራይ ፣ አማራና የአሮሚያ ክልሎች እስካሁን ድረስ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን የመኸር የሰብል ምርት መሰብሰብ መቻላቸውን የገለጹት አቶ ስዩም የደቡብና የቤንሻንጉል ክልሎች  ከ50 በመቶ በታች የሆነውን የሰብል ምርት ሰብስበዋል ብለዋል ።

በዘንድሮ የመኸር  ወቅት በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ተስማሚ የዝናብ ሁኔታ፣ የማሳ ዝግጅትና የባለሙያ ድጋፍ በመኖሩ ምክንያት በአጠቃላይ ሊሰበሰብ የታቀደው  የ321 ሚሊዮን  ኩንታል የሰብል ምርት ሊገኝ እንደሚችል ከማሳ ግምገማዎች የተገኙ ውጤቶች እንደሚያመላክቱ አቶ ስዩም ተናግረዋል ። 

በተለይ በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች የአርሶአደሩ ማሳ በድንገተኛ ዝናብ እንዳይበላሽ ተማሪዎች፣ መምህራን ፣ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ፣ ወጣቶችና  የመንግሥት ሠራተኞች  የመኸር  ምርቱን በዘመቻ በማሰባሰብ ረገድ የጎላ ሚና መጫወታቸውን አቶ ስዩም አስረድተዋል ።

ከኤል ኒኖ ክስተት ጋር በተያያዘ አምና በተፈጠረው ድርቅ ሳቢያ  የነበረውን የምርት መቀነስ ለማካካስ  በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሳምንታዊ የአየር ትንበያ መረጃዎችን በመጠቀም ለአርሶ አደሩ ተገቢው ክትትልና ድጋፍ ሲደረግ መቆየቱን አቶ ስዩም አስገንዝበዋል ።

እንደ አቶ ስዩም ገለጻ በዘንድሮ መኸር ወቅት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እርጥበት አጠር በሆኑ አካባቢዎች  ድርቅን የሚቋቋሙ ዝርያዎችን  በማቅረብ፣  ውህድ ማዳበሪያዎችና ምርጥ ዘሮችን በማከፋፈል እንዲሁም የተግባር ተኮር ሥልጠናዎች በመሠጠቱ ከዓምና አንጻር የሚገኘው ምርት  በ10 በመቶ ያድጋል ትብሎ ይጠበቃል ብለዋል ።

አጠቃላይ የአገሪቱ ያለው የ30 በመቶ የምርት ብክነት ለመቀነስ አርሶአደሩ  ዘመናዊ  የምርት አያያዝ  ዘዴዎችን መጠቀም እንዳለበትም  አቶ ስዩም አሳስበዋል ።

የቀረውን የመኸር ሰብል ምርት የአሰባሰብ ሂደትን በተጠናከረ ሁኔታ ለማስቀጠልም አርሶአደሩ  ትኩረት ሠጥቶ እንዲንቀሳቀስ አቶ ስዩም ጥሪ አቅርበዋል ።