መገናኛብዙኋን የአርብቶአደሩን ኑሮ ለመቀየር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተመለከተ

መገናኛ ብዙኋን የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለመቀየር ጉልህ ድርሻ እንዳለው ተመለከተ

ይህ የተመለከተው ከታህሳስ 7 አስከ 9 /2009 ዓመተ ምህረት ድረስ የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ጉዳዮች ሚኒስቴር ከፌደራልና ከክልሎች የተውጣጡ የኮሚኒኬሽንና የሚድያ አካላት ጋር በአዳማ ከተማ በተዘጋጀው የምክክር መድረክ ላይ ነው ፡፡

በመድረኩ በአገሪቱ በአፋር፣በኢትዮጵያ ሶማሌ ሙሉ በሙሉ እና በደቡብ በጋምቤላና በኦሮሚያ ክልሎች በከፊል ከ10 ሚሊየን በላይ አርብቶ አደሮች መኖራቸውን ነው የተጠቀሰው ፡፡

ኑሮአቸው በእንስሳት እርባታ ላይ የተመሰረተው አርብቶ አደሮች የዕምቅ ተፈጥሮ ሃብትና ተፋሰሶች ባለቤት ቢሆንም በከፍተኛ ድርቅ የሚጠቁ እና የተፈጥሮ ሃብት የሚባክንባቸው መሆኑን ተገልጿል ፡፡

እነዚህም በእንስሳት እርባታ ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መንግስት እያደረገ ባለው ጥረት በአነስተኛ እርሻ ፣በአነስተኛ ንግድና ጨው ማምረት ላይ የማይናቅ ድርሻ እንዳላቸው በመድረኩ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ተዘራ ጌታሁን የሚኒስቴር መስሪያቤቱ የፖስቹራሊስት ፎረም ኢትዮጵያ ዳይሬክተር አስታውቀዋል ፡፡

ስለሆነም የመገናኛ ብዙኋንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የአርብቶ አደሩን ኑሮ ለማሻሻል እየተደረገ ባለው ጥረት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ተገንዝበው ልዩ ትኩረት ሊሰጡት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡

ባለሙያዎቹ በዘገባዎቻቸው የአርብቶ አደሮችን ግንዛቤ በማስፋትና ተሞክሮዎችን በማስተላለፍ ረገድ አበረታች ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን አመልክተዋል ፡፡

ስለሆነም ባለሙያዎቹ የአርብቶ አደሩን ንሮ ከመቀየር አንጻር ከሚኒስቴር መስሪያቤቱ ያላቸውን ግንኙነት በማጠናከር አርብቶ አደሩ የልማቱ ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ ይበልጥ ሊሰሩ እንደሚገባ ነው የገለጹት፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የአርብቶ አደር በዓል መነሻ ገጽታዎች፣የፌዴራል ተቋሙ ተልዕኮዎችና የአፈጻጸም ውጤቶች  እና በህገ መንግስት፣ዴሞክራሲያዊ ብሔርተኝነትና ፌደራሊዝም በሚሊ ርእሶች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዷል ፡፡

ተሳታፊዎቹም በበኩላቸው መድረኩ ስለአርብቶ አደሩ ያገኙትን ዕውቀትና ግንዛቤ ተጠቅመው በጋራ ለመስራት እንደሚጥሩ በሰጡት አስተያየት አረጋግጠዋል፡፡

የአርብቶ አደሩ አከባቢዎች ከሀገሪቱ ጠቅላላ ስፋት 61 በመቶ የሚሸፍን መሆኑ የሚታወቅ ነው ሲል ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡