ሚኒስቴሩ በ2ቢሊየን ብር የልማት ፕሮጀክቶች እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ

በሀገሪቱ በ113 የአርብቶ አደር ወረዳዎች ላይ በተመደበው ከ2 ቢሊየን 98 ሚሊየን ብር በላይ በጀት የተለያዩ የልማት ስራዎች እያከናወነ መሆኑን የፌዴራልና የአርብቶ አደር ልማት ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡

በዓፋር፣በሶማሌ ፣በደቡብና በኦሮሚያ ክልሎች በሚገኙ 113 ወረዳዎች ላይ በሶስተኛው ምዕራፍ የተላያዩ የልማት ፕሮጀክቶች ተመርጠው እየተከናወኑ መሆናቸውን በሚኒስቴሩ የአርብቶ አደር ማህበረሰብ ፕሮጀክት ኃላፊ አቶ ሰዒድ ዑመር አመልክተዋል ፡፡

በክልሎቹ በጤና፣ በትምህርት፣በአነስተኛ መስኖና በአነስተኛ ንግድ ለሚሰማሩት አርብቶ አደሮች የመደገፍ ስራ እያከናወኑ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

ዘንደሮ በአርብቶ አደር ወረዳዎቹ 1ሺ 78 የተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተከናወኑ ሲሆን ፡እስከ ጥር ወር 2009 ዓመተ ምህረት ድረስ ስራው 50 በመቶ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል ፡፡

ይስራ እቅዱ በአርብቶ አደሩ የሚወጣ ሲሆን ቅድሚያ ሊፈቱ የሚገባቸው ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቁመዋል ፡፡

አርብቶ አደሩ በጉልበቱ ከሚሳተፍበት ስራ በተጨማሪ የባለቤትነት ስሜት እንዲኖረው የፕሮጀክቱ 5 በመቶ በጥሬ ገንዘብ እንዲያዋጣ እንደሚደረግ አቶ ሰዒድ አስረድተዋል ፡፡

ባለፈው ዓመት በአርብቶ አደሮች ወረዳዎች ለማከናወን ከታቀዱት 763 የልማት ፕሮጀክቶች ውስጥ 615 ተጠናቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በአገሪቱ አርብቶ አደር አከባቢዎች እ ኤ አ ከ2003 እስከ 2018 እይተከናወኑ በ4 ቢሊየን ብር በጀት ከ6ሺ በላይ ፕሮጀክቶች እንደሚከናወኑ አመልክተዋል ፡፡

በዚሁም በክልሎቹ ከሚገኙ ከ10 ሚሊየን በላይ አርብቶ አደሮች ውስጥ 4ነጥብ 5 ሚሊየን ህዝብ ተጠቃሚ እንደሚሆን ለማወቅ መቻሉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ፡፡