ኢትዮጵያ ከሳምንታት በፊት ሜክሲኮ በተካሄደው የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የብዝሃ ሕይወት ጉባኤ ላይ በብዝሃ ህይወት ከበለፀጉ አገራት ተርታ እንድትሰለፍ መደረጉ ልዩ የቴክኒክና የፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስገኝላት የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ ።
የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚንስትር ዶክተር ገመዶ ዳሌ ዛሬ በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዓለም በብዝሃ ህይወት እውቅና ከተሠጣቸው አገራት መካከል በ19ኛነት መመዝገቧና እውቅና ማግኘቷ የብዝሃ ህይወት ሃብቷን ይበልጥ ለማልማት የሚያግዝ የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ እንድታገኝ ያስችላታል ።
ኢትዮጵያ የተለየ የብዝሃ ሕይወት ክምችት ባለቤት በመሆኗ የያዘችው እምቅ ሃብት እንዳይጠፋ ልዩ ቴክኒካዊና የፋይናንስ ድጋፍ የማግኘት መብት የሚሠጣት ከመሆኑ በተጨማሪ ለአገሪቱ ገጽታ ግንባታና በዘርፉ ያላትን ተሰሚነት የሚያሳድግ መሆኑን ዶክተር ገመዶ ዳሌ አመልክተዋል ።
በሜክሲኮ ጉባኤ የኢትዮጵያ መብትና ጥቅም ከማስከበር አኳያ በአገር ደረጃ ከጉባኤው ጎን ለጎን የተለያዩ ድርድሮች መካሄዳቸውን የገለጹት ዶክተር ገመዶ ኢትዮጵያ በብዝሃ ህይወት ያላት ምርጥ ተሞክሮ በምሳሌነት ለሌሎች አገራት አቅርባለች ።
ኢትዮጵያ 6ሺ 500 የእጽዋት ሃብት ፣ 320 የእጥቢ እንስሳትና 926 የአዕዋፋት ሃብት ባለቤት በመሆኗ በብዝሃ ህይወት ከበለጸጉ አገራት መካከል አንዷ እንድትሆን ትልቅ ማሳመኛ ምክንያት መሆኑን ዶክተር ገመዶ አብራርተዋል ።
ማህበረሰብ ዓቀፍ የሆኑ የብዝሃ ህይወት ማከማቻ ባንኮችና ማዕከላት በተለያዩ አገሪቱ አካባቢዎች መቋቋማቸውን ሌላው በጉባኤውን ቀልብ የሳበና ኢትዮጵያም በብዝሃ ህይወት ከበለጸጉ አንዷ እንድትሆን እውቅና ያሠጣት ተግባር መሆኑን ዶክተር ገመዶ አያይዘው ገልጸዋል ።
ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የተጎዱ አካባቢዎችን በብዝሃ ህይወት ማበልጸግ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወት በመግለጫው ተመልክቷል ።
በቅርቡ በሜክሲኮ ካንኩን በተካሄደው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የብዝሃ ህይወት የሚኒስትሮች ጉባኤ “ ብዝሃነትን ማካተት ለሁሉም ድህንነት ” በሚል መሪ ቃል የተካሄደ ሲሆን 37 ውሳኔዎች መተላላፉን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።