የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልል መንግሥት 4ነጥብ 3 ሚሊዮን የሚሆኑ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሠማሩና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ አቅዶ እየሠራ እንደሚገኝ አስታወቀ ።
የአሮሚያ ክልል የወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሃብታሙ ሃብተ ሚካኤል እንደገለጹት የክልሉ መንግሥት በመጪዎቹ አምስት ዓመታት በማኑፋክቸሪንግ፣ በኮንስትራክሽን፣ በአገልግሎት፣ በግብርናና በንግድ ዘርፎች እንዲሠማሩ ይደረጋል ።
ክልሉ ወጣቶችን በተለያዩ አዳዲስ የሥራ ዘርፎች እንዲሠማሩ ለማድረግ እስካሁን ድረስ 107 የሥራ አይነቶችን መለየቱን የገለጹት አቶ ሃብታሙ የወጣቶች ኢኮኖሚያዊ ችግር ለመፍታት የሚያስችል እንደሆነ ታምኖበታል ብለዋል ።
በዘንድሮ የበጀት ዓመት በአጠቃላይ 1ነጥብ 5 ሚሊዮን የሚደርሱ በገጠርና በከተማ የሚገኙ ወጣቶች ተደራጅተውም ሆነ በግል በተለያዩ ሥራዎች እንዲሠማሩ ለማድረግ ባለፈው ክረምት ወቅት የተለያዩ አጫጭር ሥልጠናዎች ተሠጥተዋል ።
የኦሮሚያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ የወጣቶችንና የሴቶችን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከአዲሱ የወጣቶች የልማትና የዕድገት ፓኬጅ የመነጨ ቀመር በማዘጋጀት ወጣቶችን የሚያሳትፍ ንቅናቄ በቅርቡ ለማካሄድ ዝግጅቶችን ማጠናቀቁን አቶ ሃብታሙ አስረድተዋል ።
የክልሉ መንግሥት ለወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ 1ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር መመደቡን የገለጹት አቶ ሃብታሙ በፌደራል ደረጃ የሚመደበው የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ተጨማሪ የፋይናንስ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል ።
የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት በአሁኑ ወቅት በክልሉ በአጠቃላይ ምን ያህል ሥራ አጥ ወጣቶች እንደሚገኙ የሚገልጽ መሠረታዊ መረጃዎች በመሰብሰብና ጥናቶችን በማካሄድ ላይ እንደሚገኝ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።