ሚኒስቴሩ 3ነጥብ 47 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት መገኘቱን አስታወቀ

በአዲስ አበባና በአምስት ክልሎች 3 ነጥብ 47 ቢሊዮን ሊትር ወተት ተመርቶ   ለህብረተሰቡ ፍጆታነት መዋሉን  የእንስሳትና  ዓሳ ሃብት  ሚኒስቴር  አስታወቀ ።  

በሚኒስቴሩ የወተት ሃብት ልማት ዳይሬክተር አቶ ታሪኩ ተካ እንደገለጹት፤ በግማሽ  በጀት ዓመቱ ከአዲስ አበባ ከተማ ፣ ከትግራይ ፣ ከአማራ ፣ ከኦሮሚያ ፣ ከደቡብና ከቤኒሻንጉል ክልሎች 3 ነጥብ 47 ቢሊዮን ሊትር ወተት ተመርቶ ለህብረተሰቡ ፍጆታነት ውሏል።

በአገሪቱ የወተት ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተለያዩ ፓኬጆቹም ተግባራዊ መደረጋቸውን የገለጹት አቶ ታሪኩ ፤በተለይ 279 ሺ  የሚደረሱ ለአርሶና አርብቶ አደሮች የኤክስቴንሽን አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ተችሏል ።

እንደ አቶ ታሪኩ ገለጻ በአሁኑ ወቅት አርሶ አደሩም፤ አርብቶ አደሩና ወጣቱ የወተት ምርትን  ለገበያ በማቅረብ  የተሻለ  ገቢ  በማግኘት ተጠቃሚነቱን  ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ምርቱ  ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ።

በአገሪቱ የተሻለ የወተት ምርት የሚሠጡ የእንስሳት ምርጥ ዝርያዎችን የማዳቀል አገልግሎት የሚሠጠው አንድ  ማዕከል ብቻ እንደነበር  የጠቆሙት ዳይሬክተሩ፤ በአሁኑ ወቅት ማዳቀያ ማዕከላት በመቀሌ ፣ በነቀምት በሐዋሳና በባህርዳር ከተሞች ተገንብተው አገልግሎት መሥጠት መጀመራቸውን አስታውቀዋል ።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ አንዲት ላም በቀን በአማካኝ 1ነጥን 37 ሊትር ወተት  እየሠጠች መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ከአንዲት ላም በአማካኝ  በቀን የሚገኘው የወተት ምርት   6  ሊትር ለማድረሰ አቅዶ እየሠራ መሆኑን አቶ ታሪኩ አስረድተዋል ።

በኢትዮጵያ ከሏት 57 ሚሊዮን የቁም እንስሳት ውስጥ 10 ሚሊዮኑ ወተት የሚሠጡ መሆናቸውን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።