የታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ በጉራጌና በስልጤ ዞኖች በነበረው የአንድ ወር ቆይታ 111 ሚሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክር ቤት የህዝብ ተሳትፎ ማስተባባሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ ።
የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አብርሃም ለዋልታ እንደገለጹት ፤ዋንጫው በጉራጌ ዞን በነበረው ቆይታ ከህብረተሰቡ 60 ሚሊዮን ብር ከስልጤ ዞን ደግሞ 51 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል ።
በስልጤ ዞን የአገር ሽማግሌዎች የህዳሴውን ዋንጫና ከብቶች ይዘው በመሄድ ለጉራጌ ዞን ህዝብ በስጦታነት ያበረከቱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ይህም ተግባር የሁለቱን ህዝቦች አንድነት ለማሳየትና ወዳጅነት ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ነው ያስረዱት ።
የታላቁ ህዳሴ ዋንጫ የብሔራዊ አንድነት መገለጫ መሣሪያ መሆኑንና ሁሉም የአገር ዜጋ ለታላቅ ፕሮጀክቱ ድጋፍ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያበረክት የሚያግዝ መሆኑን አቶ ኃይሉ አብራርተዋል ።
የህዳሴው ዋንጫ የብሔራዊ አጀንዳዎችን ለማሳካትና በአገር ውስጥ የይቻላል መንፈስ እንዲሰርጽ ታላቅ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ አንሰተዋል ።
የታላቁ የህዳሴ ግድብ ለአንድ ዓመት ያህል በኦሮሚያ ክልል በሁሉም ዞኖች ቆይታው ካደረገ በኋላ ከወር በፊት ወደ ደቡብ ክልል የተለያዩ ዞኖች በመዘዋወር ገቢ እያሰባሰበ ይገኛል ነው ያሉት ።
እንደዚሁም የህዳሴው ዋንጫ በኦሮሚያ ክልል ቆይታው 607 ሚሊዮን ብር ፣ በአማራ ክልል 432 ሚሊየን ብር፣ በትግራይ ክልል 81 ሚሊዮን ብር ፣ በአፋር ክልል 71 ሚሊዮን ብርና በቤንሻንጉል ክልል 33 ሚሊዮን ብር ገቢ ማሰባሰብ መቻሉን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው ጠቅሰዋል ።
በአጠቃላይ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል ከህብረተሰቡ ከ9 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡንም አስታውሰዋል ።
( ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ )