ኢትዮጵያ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረምን ለማስተናገድ ጥያቄ አቀረበች

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ የሚመክረውን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም ለማስተናገድ በይፋ ጥያቄ አቀረበች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በዳቮስ ስዊዘርላንድ ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም መስራችና ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፕሮፌሰር ክላውስ ማርቲን ሽዋብ ጋር ተነጋግረዋል።

በተጨማሪም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከማይክሮሶፍት መሥራችና ባለቤት ከቢሊዬነሩ ቢል ጌትስ ጋር በዳቮስ ምክክር አካሂደዋል። 

በዚሁ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ ከዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ጋር ያላት ስትራቴጂያዊ ግንኙነት አጠናክራ ትቀጥላለች።

ይህን ግንኙነቷን ለማጎልበትም እኤአ በ2018 በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚመክረውን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረምን ለማስተናገድ በይፋ ጥያቄ አቅርበዋል።

ቀደም ሲል ኢትዮጵያ የዓለም ኢኮኖሚ ፎረምን የአፍሪካን መዋቅራዊ ሽግግር መልክ ማስያዝ በሚል ጭብጥ እኤአ በ2012 በአዲስ አበባ በብቃት ማስተናገዷን አውስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ካለፉት ሁለት አሥርት ዓመታት አንስቶ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ዕድገት ለፕሮፌሰር ሽዋብ አብራርተውላቸዋል። 

ፕሮፌሰር ክላውስ ሽዋብ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ኢትዮጵያ እያስመዘገበች ያለውን ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም በቅርበት እየተከታተለው ነው።

አገሪቷ እያስመዘገበች ያለው ፈጣን ዕድገት ለሌሎች ታዳጊ አገሮች በአርአያነት የሚጠቀስ እንደሆነም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ያቀረበቸው ጥያቄ በደቡብ አፍሪካ ደርባን በሚካሄደው ስብሰባ በፎረሙ የአሰራር ሥርዓት መሰረት ምላሽ እንደሚያገኝ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ 22ኛውን የዓለም ኢኮኖሚ ፎረም የአፍሪካ ጉዳዮች ዘርፍን በስኬት ማስተናገድ መቻሏም ታሳቢ እንደሚደረግ አመልክተዋል።

በተለይ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊና አሕጉራዊ ጉባዔዎችን በማስተናገድ በኩል ያላት ብቃትና ዝግጁነት ፎረሙን እንድታዘጋጅ ሊያስመርጣት እንደሚችል ነው ፍንጭ የሰጡት።

በተመሳሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ከማይክሮሶፍት መሥራችና ባለቤት ከቢሊዬነሩ ቢል ጌትስ ጋር በዳቮስ ምክክር አካሂደዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት እንዳገለጹት፤ ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ የኢንፎርሜሽን ኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂ ወይም አይ.ቲ ፓርክ እያቋቋመች ነው።

በዚህ ወጣቶችን ተጠቃሚ በሚያደርገው ፓርክ የማይክሮሶፍት ተሳትፎና ድጋፍ አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።

ባለሀብቱ ቢል ጌትስም ለአዲስ አበባ አይ.ቲ ፓርክ ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን ውይይቱን የተከታተሉት በስዊዝርላንድ የኢትዮጵያ አምባሳደር ነጋሽ ክብረት አስረድተዋል።

ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን እኤአ በ2012  ጽህፈት ቤቱን በአዲስ አበባ ከፍቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

ቢሊዬነሩ ቢል ጌትስ ባለፈው ሐምሌ ወደ አዲስ አበባ በመጡበት ወቅት በኢትየጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት ለማሳደግ እንደሚፈልጉ መግለጻቸው ይታወሳል።

በፋይናንስ አገልግሎት በተለይ ደግሞ በሞባይል የባንክ አገልግሎት ዙሪያ በገጠራማ የአገሪቷ አካባቢ በስፋት መንቀሳቀስ እንደሚፈልጉ ገለጸዋል።

ቢል ጌትስ ከኢትዮጵያ ጋር ያላቸውን አጋርነት ወደፊትም ተጠናክሮ ለማስቀጠል ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል-(ኢዜአ)።