ኤጀንሲው አርሶአደሩ ተገቢውን የምርቱ ዋጋ እንዲያገኝ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

አርሶአደሩ የግብርና ምርቱ  ተገቢው ዋጋ እንዲያገኝ ለማድረግ  የተለያዩ ሥራዎችን  እያከናወነ እንደሚገኝ የፌደራል ህብረት ሥራ ኤጀንሲ አስታወቀ ።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ ኡስማን ስሩር ለዋልታ እንደገለጹት ፤በ2008/09 ምርት ዘመን ከፍተኛ የግብርና ምርት በመገኘቱ ምክንያት የግብርና ምርት ዋጋ ወርዶ በአርሶ አደሩ ላይ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እንዳያስከትል ዘርፈ ብዙ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ።

በአገሪቱ የሚገኙ የመሠረታዊ ህብረት ሥራ ማህበራት አርሶ አደሩ የሰበሰበውን የሰብል ምርት በተመጣጣኝ ዋጋ በመግዛት ለሸማቹ የህበረተሰብ ክፍል ተመጣጣኝ በሆነ ዋጋ እንዲቀርብ ለማድረግ ዝግጅቶች እየተጠናቀቁ መሆኑን አስረድተዋል ።

ኤጀንሲው ከገዛው የሰብል ምርት ትርፍ የሆነውን ለኢትዮጵያ እህል ንግድ ድርጅት ፣ ለዓለም የምግብ ፕሮግራምና ለሌሎች አካላት ለመሸጥ ዝግጅት ማድረጉን ነው የጠቆሙት ።

በተጨማሪም የህብረት ሥራ ማህበራት የግብርና ምርትን ከሚያቀነባብሩ የተለያዩ የፓስታ፣ የዱቄትና የቢራ ፋብሪካዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር የስንዴና የገብስ አምራች አርሶ አደሮች የተሻለ ገቢ እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑን አቶ ኡስማን አስታውቀዋል ።     

እንደ አቶ ኡስማን ማብራሪያ የህብረት ሥራ ማህበራት የሚያጋጥማቸውን የመጋዘን ችግር ለመፍታት  በዘንድሮ የበጀት ዓመት 68  ሚሊዮን  ብር  በሆነ  ወጪ በተለያዩ  ክልሎች  ከ 5 ሺ ኩንታል  በላይ  የመያዝ አቅም ያላቸው መጋዝኖች ተገንብተዋል ።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 78 ሺህ 900 መሠረታዊ  ህብረት ሥራ ማህበራት ፣373  የህብረት ሥራ ዩኒየኖች 17 ነጥብ 6  ቢሊዮን ብር  ካፒታል እያንቀሳቀሱ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።  

ከዘንድሮ የመኸር ምርት 320 ሚሊየን ኩንታል  ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ መገለጹ ይታወቃል ፡፡