የዳቮስ ዓለም አቀፍ ፎረም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገጽታ ከማስተዋወቅ ባለፈ አፍሪካዊ ሁኔታን ማስረዳት የተቻለበት እንደሆነ የኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ገለጹ።
በዳቮስ ስዊዘርላንድ ሲካሄድ የቆየው 47ኛው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ከተጠናቀቀ በኋላ ጠቅላይ መኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ትክክለኛ ገጽታ በመሰተዋወቅ ዕድል በመፈጠሩ የዓለም አቀፍ ግዙፍ ኩባንያዎችና ባለኃብቶች በሀገራችን በኢንቨስትመንት መስክ ለመሰማራት እንዲዘጋጁ አስችሏል ።
ኢትዮጵያ በፎረሙ በተከታታይ የመሳተፏ ዋናው ምክንያት በልማት፣ በዴሞክራሲና በአገራዊ ግንባታ ሥራዎቿ ዓለም አቀፋዊ ዕይታ እንዲኖራት ለማድረግ መሆኑን አስረድተዋል ።
ይህ ደግሞ ኢትዮጵያ ውጤታማ ባለኃብቶችን በመሳብ የኢንቨስትመንት ፍሰቷን ለማሳደግ የሚረዳት መሆኑን አመልክተዋል ።
ፎረሙ በአንድ በኩል የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና አፍሪካዊ ሁኔታን ማስረዳት በሌላ በኩል የዓለምን አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለመረዳት የተቻለበት እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚንስትሩ የጠቆሙት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከስዊዘርላንድ ኮንፌደሬሽን ፕሬዝዳንት ዶሪስ ሊዩትሃድና ከጊኒ ፕሬዚዳንት አልፋ ኮንዴ ጋር የተነጋገሩ ሲሆን ፤ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ፒንግና ከእንግሊዟ ጠቅላይ ሚኒስትር ቴረዛ ሜይ ጋርም አጭር ውጤታማ ቆይታ ማድረጋቸውን አብራርተዋል ፡፡
ፎረሙ ኢትዮጵያ ሁለንተናዊ የዲፕሎማሲ ጥረቷ የተሳካ እንደነበር የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስት፤ይህም ግንኝነቱን መነሻ አድርጎ የኢትዮጵያን ፖሊሲ ለመቃኘት የሚያስችል እንደሆነ አመልክተዋል ።
ከሁሉም በላይ በአገራዊ የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም አስረድተዋል።
ፎረሙ የኢትዮጵያን ተደማጭነት ለማሳደግ የሚረዳ በመሆኑ አገሪቱ ከፎረሙ ጋር የጀመረችው ትስስር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዓለም ኢኮኖሚ ፎረም መስራችና ዋና ሥራ አሥፈፃሚ ከፕሮፌሰር ክላውስ ሽዋብ ጋር ምክክር አድርገዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣዩ የፈረንጆች ዓመት በአፍሪካ ጉዳዮች አተኩሮ የሚነገጋረውን የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም ለማስተናገድ በይፋ ጥያቄ አቅርባለች።
ፕሮፌሰር ሽዋብ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት ኢትዮጵያ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ2012 ያስተናገደችው የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም እስከ ዛሬ በአፍሪካ ከተካሄዱት ምርጡ ነው።
እናም አገሪቱ ይህን ልምዷን በመጠቀም ፎረሙን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላት ነው ያስገነዘቡት።
ይህም አገራዊ የገጽታ ግንባታ ለመፍጠር ተጨማሪ ዕድል የሚፈጥር ነው ብለዋል ።
በሌላ በኩል በዳቮስ የዓለም የኢኮኖሚ ፎረም የተሳተፉ ግዙፍ ኩባንያዎች ኢትዮጵያ በኢንቨስትመንት ለመሰማራት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
ከኢትዮጵያ ጋር በአጋርነት የሚሰሩ እንደ ቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን ያሉ ተቋማት አጋርነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
ከተለያዩ ባለኃብቶችና ኩባንያዎች በመነጋገር መግባባት ላይ ደርሳለች።
ኢትዮጵያ በአገር ውስጥ እንዲመረት ለማድረግ በፋርማሲዩቲካል ኢንዱስትሪ መስከ በርካታ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች ጋር በዳቮስ ምክክር ተደርጓል ብለዋል ።
ኢትዮጵያ ከአጠቃላይ የፋርማሲዩቲካል ፍጆታዋ 20 በመቶውን ብቻ በአገር ውስጥ የምታመርት ሲሆን ቀሪውን 80 በመቶ ከውጭ በግዢ እንደምታስገባ በመጠቆም ።
ሌላው የትኩረት መስክ የነበረው በመረጃ መረብ አቅምን በማጎልበት ለአገራዊ ልማትና ለሕዝቡ ተጠቃሚነት ማዋል ነው።
በዚህ በኩል በሞባይል ንግድና በሞባይል ባንኪንግ ሥርዓት አገሪቱን ለመደገፍ ስምምነት ላይ መደረሱን ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት ።
በጤና መስክ የተጀመሩ ሥራዎችን ይበልጥ ለማስፋፋት የተጠናከረ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ስምምነትም ተደርሷል ብለዋል ።
እናም ኢትዮጵያ በፎረሙ ያደረገችው ተሳትፎም የተሳካ እንደነበር ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹት ።
ፎሮሙ ወሳኝ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገበት መሆኑንም ጠቁመዋል ።
በተለይ የዶናልድ ትራምፕ ወደ አሜሪካ አስተዳደር መምጣት በፎረሙ የተለያዩ መድረኮች ውይይት ሲደረግበት እንደነበር ጠቅሰዋል።
የትራምፕ መምጣት ብዙዎቹ እንደሚያስቡት ጨለምተኛ እንዳልሆነና ይልቁንም የዓለም ኢኮኖሚ መነቃቃት እንደሚታይበት የሥነ-ምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች ትንታኔ አቅርበዋል ነው ያሉት ።
በተለይ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም ዳይሬክተር ክሪስቲን ላጋርድ ያቀረቡት ትንታኔ አበረታች እንደሆነ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያመለከቱት(ኢዜአ) ።