የአዲስ አበባ ጅቡቲ ምድር ባቡር በየካቲት ወር መጨረሻ አገልግሎት እንደሚጀምር የኢትዮጵያ የምድር ባቡር ኮርፖሬሽን አስታወቀ ።
ኮርፖሬሽኑ ዛሬ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግስት የልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስድስት ወራት የስራ አፈጻጸም ሪፖርቱን አቅርቧል።
የኮርፖሬሽኑ ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ኢንጅነር ጌታቸው በትሩ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን ጨምሮ የመስመሩ ሙከራ እየተጠናቀቀ መሆኑን አመልክተዋል።
የኤሌክትሪክ አቅርቦት እና የባቡር ጣቢያዎችን ከዋና ዋና መንገዶች ጋር የሚያገናኙ መንገዶች ግንባታ እየተጠናቀቀ መሆኑን አብራርተዋል።
ባለፉት ሶስት ወራትም መስመሩን የመሞከሩ ተግባር ሲከናወን መቆየቱን ጠቅሰዋል።
የምድር ባቡር መስመሩ ሀገር አቋራጭ በመሆኑም በኢትዮጵያ እና ጅቡቲ መካከል የጋራ ግንኙነት ሰነድ መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
የባቡር መስመሩን የሚያስተዳድር ኩባንያ ለመምረጥ ከስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነው ያስረዱት።
ሁለቱን ሃገራት በባቡር ለማስተሳሰር የተዘረጋው መስመር ከአዲስ አበባ ጅቡቲ ድረስ 752 ኪሎ ሜትር ርቀትን ይሸፍናል።
ከዚሁም ውስጥ ኢትዮጵያ በ3 ነጥብ 4 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ወጪ የገነባችው 656 ኪሎ ሜትር መስመር መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም በይፋ መመረቁ ይታወቃል ።
ከታላቁ የህዳሴ ግድብ ቀጥሎ ሁለተኛው ግዙፍ ፕሮጀክት የሆነው የምድር ባቡር መስመሩ ከ2 ሺህ በላይ ኢትዮጵያውያንን መቅጠሩንም ነው የተመለከተው ።
በጅቡቲ መንግሥት በኩል የተገነባውና 104 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው መስመር ጥር 2 2009 በይፋ መመረቁ አይዘነጋም-(ኤፍ.ቢ.ሲ)።