በአገሪቱ የሥራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ ።
በሚኒስቴሩ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ናስር ለገሰ ለዋልታ እንደገለጹት በአገሪቱ የወጣቶች የሥራ አጥነትን ችግር ለማስወገድ የሚያስችለውን የወጣቶች የተንቀሳቃሽ ፈንድ ጥቅም ላይ ለማዋል ከወረዳ ጀምሮ የሥራ አጥ ወጣቶችን የመለየት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል ።
የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር በአገሪቱ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር ለማስወገድ በከተማና በገጠር በተለያዩ ዘርፎች ላይ የሥራ ፈጠራ ለማበረታታት የተለያዩ ቅድመ ዝግጅቶች እያካሄዱ መሆኑን አቶ ናስር ተናግረዋል ።
የአገሪቱ ወጣቶች ስኬታማ የሚያደርጓቸውን የሥራ መስኮች በመለየትና የሚያጋጥሟቸውን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች በአሁኑ ወቅት እየተሠጣቸው መሆኑ ተመልክቷል ።
በመላ አገሪቱ እየተካሄዱ ባሉት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥልጠናዎች የተለያዩ የወጣቶች አደረጃጀቶች በወጣቶች የዕድገትና የለውጥ ፓኬጅና የወጣቶች ስትራቴጂዎች ላይ በመወያያት መግባባት ላይ ለመድረስ ውይይት እያካሄዱ ይገኛል ተብሏል ።
ወጣቶች ከተንቀሳቃሽ ፈንዱ ተጠቃሚ የሚሆኑት ለሚሠማሩበት የሥራ መስክ የሚውለውን 10 በመቶ ገንዘብ በጋራ በመሆን በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ሲቆጥቡ መሆኑን አቶ ናስር ጠቁመዋል ።
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በሚገኙባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ወጣቶች ቀሪውን የብድር ገንዘቡን ከንግድ ባንክ ማግኘት እንደሚችሉ የሚገልጹት አቶ ናስር የንግድ ባንክ በማይገኙባቸው የገጠር አካባቢዎች በማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ብድር ይመቻችላቸዋል ብለዋል ።
በገጠርና በከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ቢያንስ አምስት ሆነው በመደራጀት አዋጭ በሆኑ የሥራ ዘርፎች ለመሠማራት የራሳቸውን ፕሮጀክት በመቅረጽናበማቅረብ መንግሥት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ከመደበው የወጣቶች ተንቀሳቃሽ ፈንድ ተጠቃሚ መሆን እንደሚችሉ ተመልክቷል ።
በአገሪቱ የሚገኙ ወጣቶች በመንግሥት የቀረበውን የተንቀሳቃሽ ፈንድ በመጠቀም በተለያዩ አማራጭ የሥራ መስኮችን ላይ በመሠማራት የራሱን የኢኮኖሚያዊ አቅም ከማሳደግ ባለፈ ለአገር ዕድገት አስተዋጽኦ እንዲያበረክት አቶ ናስር ጥሪ አቅርበዋል ።