የታዳሽ የኃይል ምንጭን ማልማት የአፍሪካን የኢንዱስትሪ ዕድገት ለማፋጠን ያግዛል- ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም

አፍሪካ ያላትን እምቅ የታዳሽ የኃይል ሃብት በአግባቡ እንድታለማ ማድረግ በአህጉሪቱ  የኢንዱስትሪ ዘርፉ ዕድገትን ለማፋጠን እንደሚያስችልና  ዘላቂነት  ያለው  የልማት  ግቦችን  ለማሳካት  እንደሚያስችላት  ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተናገሩ ።    

ጠቅላይ ሚንስትሩ ትናንት ከ28ኛው የአፍሪካ መሪዎች መደበኛ ስብሰባ ጋር በተያያዘ  በተካሄደው የአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ፎረም ላይ  ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት አፍሪካ ያላትን የታዳሽ የኃይል ምንጭ በአግባቡ ሳትጠቀም  ኢንዱስትሪን ማስፋፋት እንደሚያዳግታት ተናግረዋል ።    

በታዳሽ ኃይል ልማት ላይ ያተኮረው ጉባኤን የመሩት ተሰናባቿ የአፍሪካ ህብረት  ሊቀመንበር  ዶክተር ዲላሚኒ ዙማ ፣ የአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዚደንት አክኑዋሚ አዴሲ ሲሆኑ  ሌሎች የአህጉሪቷ  የልማት አጋር አገራት የሆኑት ፈረንሳይ ፣ ጀርመንና የአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ተገኝተዋል ።

እንደ ጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ገለጻ ኢትዮጵያ በአፍሪካ የታዳሽ ኃይል ኢኒሺየቲቭ የምስራቅ አፍሪካን የምትወክል መሆኗንና  የታዳሽ የኃይል  ምንጭ  በአፍሪካ  ይበልጥ  እንዲስፋፋ  በትኩረት እየሠራች ትገኛለች ።   

የአፍሪካ ልማት ባንክ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክትን እውን እንዲሆኑ የበኩሉን  ድጋፍ  እያደረገ  መሆኑን  ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመው  በአፍሪካ  የዘላቂ የልማት ግቦች በፍጥነት እንዲሳኩ ለማድረግ  የታዳሽ የኃይል ምንጭ ፕሮጀክቶችን በአጭረ ጊዜ ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆኑ  መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል ።

የአፍሪካ  ህብረት ሊቀመንበር ዶክተር ድላሚኒ ዙማ የታዳሽ ኃይል ፕሮጀክቶችን በአፍሪካ ተግባራዊ መደረጋቸው በአህጉሪቱ የወጣቶችን የሥራ አጥነት ችግር በመቅረፍና የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦትን በማሳደግ  በኩል አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አስገንዝበዋል ።

የአፍሪካ  የታዳሽ ኃይል  ኢኒሺየቲቭ የተቋቋመው በአፍሪካ  የታዳሽ  ኃይል  ምንጭን በማስፋፋት እኤአ በ2020  የካርቦን ልቀትን  በመቀነስ እኤአ ከ 2016 እስከ 2020 ድረስ  5 ቢሊዮን  የአሜሪካ ዶላር  ገቢ ለማግኘት  ዓላማ ሰንቆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ።

( ትርጉም :  በሰለሞን ተስፋዬ )