የሚገነቡ ህንፃዎች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ሚኒስቴሩ የተጠናከረ ቁጥጥር ሊያደርግ ይገባል-ምክር ቤቱ

የኮንስትራክሽን ሚኒስቴር የሚገነቡ ህንፃዎች የጥራት ደረጃቸው የተረጋገጠ እንዲሆን በማድረግ በኩል የቁጥጥር ሥራውን ሊያጠናክር ይገባል ተባለ።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማና ኮንስትራክሽን ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚኒስቴሩን የስድስት ወራት ዕቅድ አፍፃጸምን ዛሬ ገምግሟል።

ቋሚ ኮሚቴው የኮንስትራክሽን ግንባታዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ ያለመጠናቀቅና የጥራት ጉድለት ችግር እንደሚስተዋልባቸው ገምግሟል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ፋፊ ዲልጋሳ በዚሁ ጊዜ እንዳሉት አዲስ የሚገነቡና የጥገና አገልግሎት የሚያስፈልጋቸው ህንፃዎች ፍጥነትና የጥራት ደረጃቸውን ጠብቀው መገንባታቸውን ሚኒስቴሩ በፍተሻና ቁጥጥር ሥራ ሊያረጋግጥ ይገባል።

ሚኒስቴሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የመንግሥት ነባር ግንባታዎችና አዳዲስ ፕሮጀክቶች ጥራታቸውን ጠብቀውና በወቅቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸው የማረጋገጥ ኃላፊነቱን በትኩረት እንዲወጣ አሳስበዋል።

የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትሯ ወይዘሮ አይሻ መሐመድ በሰጡት ማብራሪያ ለግንባታዎቹ መጓተት የሙያተኞች እጥረት፣ የግብዓትና የፋይናንስ ችግር በምክንያትነት አንስተዋል።

የሚገነቡ ህንፃዎች የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑና በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ ከሚመለከታቸው ፈፃሚና አስፈፃሚ አካላት ጋር በቅንጅት ለመሥራት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል።

ከቋሚ ኮሚቴው የተሰጠው ግብረ መልስ ገንቢ በመሆኑ ሚኒስቴሩ በቀጣይ በትኩረት ተግባራዊ እነደሚያደርግም አረጋግጠዋል። (ኢዜአ)