የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዘንድሮ የበጀት ዓመት ስድስት ወራት ውስጥ 82 የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ምክረ ሓሳቦችን በማውጣት ለተጠቃሚዎች ማሠራጨቱን ገለጸ ።
በኢንስቲትዩቱ የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ፍሰሃ ዘገየ ለዋልታ እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ 70 የተለያዩ የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ምክረ ሓሳቦችን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ ታቅዶ 82 የሚደርሱትን ማቅረብ ችሏል ።
ኢንስቲትዩቱ አዳዲስ የሚወጡ የግብርና ቴክኖሎጂና ምክረ ሓሳቦችን በተሻለ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ በግማሽ ዓመቱ 21ሺ 709 አርሶና አርብቶ አደሮችን ለማሠልጠን አቅዶ 23 ሺ 920 የሚሆኑት በቴክኖሎጂ ማላመድ ሥልጠና እንዲያገኙ ተድርጓል ።
በአገሪቱ የጥጥ ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ ቴክኖሎጂዎችን ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ኢንስቲትዩቱ ተባዮችን የሚቋቋም ምርጥ የጥጥ ዝርያን ለማሠራጨት በወረር ፣ ተንዳሆ፣ አሳይታ ፣አሞቴ፣ ውይጦ፣ አሶሳና ፓዌ የሙከራ ሥራዎች እየተካሄዱ መሆኑ አቶ ፍሰሃ አስረድተዋል ።
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት በዘንድሮ የበጀት ዓመት 586 የግብርና ቴክኖሎጂዎችና ምክረ ሓሳቦችን ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።