የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ የግብርናውን ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግረው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለጹ።
በአገር አቀፍ ደረጃ 17 የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ የሚገነባባቸው አካባቢዎች ተለይተዋል።
ከነዚህ መካከል በሙከራ ደረጃ በአማራ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብና ትግራይ ክልሎች አራት ፓርኮችን ለመገንባት ወደ ተግባር ተገብቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ከተማ ለሚገነባው የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ የመሰረት ድንጋይ ትናንት አኑረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም በወቅቱ እንደገለጹት፤ ፓርኩ ለዘመናት ከኋላ ቀር አሰራር ያልወጣውን የግብርና ዘርፍ ወደ አዲስ ምዕራፍ ያሸጋግራል።
የቡሬ ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ አንድ ሺ ሄክታር መሬት ስፋት ያለው ሲሆን፤ በቅድሚያ በ260 ሄክታር መሬት ላይ እንደሚገነባ ተገልጿል።
ፓርኩ ሲጠናቀቅ የአካባቢው አርሶአደሮች በሰፊው ከሚያመርቱት ማሽላ፣ ስንዴ፣ ሰሊጥ፣ አትክልትና ፍራፍሬ፣ ማር፣ የእንስሳት ተዋፅኦዎችና መሰል የግብርና ምርቶች በግብዓትነት በመጠቀም እሴት ጨምሮ ለውጭ ገበያዎች የሚያቀርብ ይሆናል።
ለፓርኩ ግንባታ የሚያስፈልገውን 184 ሚሊዮን ዶላር የፌዴራልና አማራ ክልል መንግስታት በመደቡትና ከሌሎች አለም አቀፍ የልማት ድርጅቶች በሚገኝ ድጋፍና ብድር ይሸፈናል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም፤ “ኢትዮጵያ በእንስሳት ሃብት፣ ለእርሻ ተስማሚ የሆነ መሬትና በሌሎች የግብርና ሃብቶች ከአለምና ከአህጉሪቷ ቀዳሚ ከሚባሉ አገሮች ተርታ ብንሆንም ለኢንዱስትሪዎች ግብዓት የሚውል ምርት በሚፈለገው ልክ እያመረትን አይደለም” ብለዋል።
ለዚህም በምክንያትነት የጠቀሱት አርሶና አርብቶ አደሮች በሳይንሳዊ መንገድ ያለማምረታቸውና ለተመረቱ ምርቶች የግብይት ሰንሰለቱ ዝቅተኛነት፣ በሚመረቱ ምርቶች ላይ እሴት እየጨመሩ ወደ አለም ገበያ ያለመላክ ናቸው።
የአርሶና አርብቶ አደሮችን ምርታማነትን ከሚያሳድጉ ተግባራት ጎን ለጎን ምርቶችን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ኢንዱስትሪዎች ማስፋፋት አስፈላጊ መሆኑን ያመለከቱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም በገጠር ሃብት ለመፍጠርና ኢኮኖሚው እንዳይናወጥ ለማድረግ እንደሚያስችል ተናግረዋል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ፓርኩ የአካባቢው አርሶ አደሮች ተጨማሪ የግብርና ምርቶችን እንዲያመርቱ ማስተማመኛ ከመስጠቱም በላይ በአካባቢው የምርት ዋጋ መቀዛቀዝን ያስቀራል።
ከአንድ ዓመት በኋላ ግንባታው የሚጠናቀቀው የቡሬ ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ እስከ 100 ኪሎ ሜትር ዙሪያ ያሉ አርሶ አደሮችን ምርት በግብዓትነት ይጠቀማል።
በቀጣይም መራዊ፣ እንጅባራ፣ ፍኖተ ሰላም፣ ቻግኒ፣ ዳንግላ፣ አማኑኤልና ሞጣ የገጠር የግብርና ምርቶች ማዕከል የሚቋቋሙ ሲሆን፤ የሞጣ ማዕከል ግንባታ ተጀምሯል።
ፓርኩ የሚገኝበት ምዕራብ ጎጃም ዞን በእንስሳትና ሰብል ምርቶች ከፍተኛ አቅም ካላቸው አካባቢዎች ቀዳሚ ነው።
በዓመት ከ32 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የሰብል ምርት የማምረት አቅም ሲኖረው፤ ከስድስት ሚሊዮን በላይ የእንስሳት ሃብት እንዳለው ከዞኑ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።
እንደ ርዕሰ መስተዳድሩ ፤ “ የአካባቢው አርሶ አደር ለፓርኩ ግብዓት የሚሆን ጥራትና ብዛት ያለው የሰብልና እንስሳት ምርቶችን እንዲያመርት አርሶ አደሮችና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት በቅንጅት መስራት ይኖርብናል” ብለዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ፓርኩ በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ልዩ ድጋፎችን በማድረግ የሰለጠነ የሰው ሃይል ለማቅረብ በአካባቢው ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች፣ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛና መሰል ተቋማት ከወዲሁ ዝግጅት እንዲጀምሩ አሳስበዋል።
የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ ዶክተር መብራቱ መለስ በበኩላቸው፤ "መሰል ፓርኮች የገጠር ትራንስፎርሜሽን ስራችንን በፍጥነት ለማሳካትና በክልሎች ፍትሃዊ እድገት እንዲኖር ያግዛል" ብለዋል።
የቡሬ ግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርክ ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ለ619 ሺ ሰራተኞች የስራ እድል እንደሚፈጥር ታውቋል።
በፓርኩ ተቀነባብሮ ወደ ዓለም ገበያ ከሚላከው ምርት በዓመት 14 ቢሊዮን ብር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ለሙከራ የሚገነቡ ሌሎች ሦስት የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፓርኮች በያዝነው ዓመት ወደ ግንባታ ይገባሉ።
በትግራይ ምዕራባዊ አካባቢ፣ በኦሮሚያ ክልል ልዩ ቦታው ቡልቡላና ደቡብ ክልል ይርጋለም ላይ ተመሳሳይ ፓርኮች በየካቲት የግንባታ መሰረተ ድንጋይ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።( ኢዜአ)