በግማሽ ዓመቱ 66ሺህ ቶን ማር መመረቱን ተገለጸ

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ 66ሺህ ቶን ማር ማምረት መቻሉን የእንስሳትና ዓሣ ሐብት ሚንስቴር አስታወቀ፡፡

በሚንስቴሩ የማርና ሐር ልማት ተወካይ ዳይሬክተር አቶ ደምሰው ዋቅጅራ ከዋልታ ኢንፎርሜሽ ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ባሳለፍነው መጀመሪያ ግማሽ የበጀት ዓመት 24ሺህ ቶን ማር ለማምረት ታቅዶ 66ሺህ ቶን ማር ማምረት ተችሏል፡፡

ምርቱ ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የዝናብ እጥረት ባለመከሰቱና ምርታማነትን ለማሳደግ የሥራ ላይ ሥልጠና በባለሙያዎች በታገዘ መልኩ በመሰጠቱ ምርቱ ከፍ እንዲል ምክንያት ሆኗል፡፡

ከ90 በመቶ ላይ የሚሆኑት አናቢዎች ባሕላዊ የንብ ቀፎ ይጠቀማሉ፤ የሽግግርና ፍሬም ቀፎዎችን በመጠቀም ምርታማነትን ለማሳደግ ጥረት እየደረገ እንደሆነ አቶ ደምሰው አክለው ገልጸዋል፡፡

ምንም እንኳን ምርቱ በከፍተኛ መጠን ቢጨምርም የማር ብረዛ (ማርን ከሌሎች ባዕድ ነገሮች ጋር መቀላቀል) ወደ ውጪ በመላክ የሚገኘው የውጭ ምንዛሬ እክል እየገጠመው እደሆነ ታውቋል፡፡ ለዚህም ሲባል የማር የጥራት ደረጃን የሚያስጠብቅና ማርን በመበረዝ ወደ ገበያ የሚያወጡ ግለሰቦችንና ድርጅቶችን ተጠያቂ የሚያደርግ በአዋጅና ደንቡ መሰረት የአፈፃፀም መመሪያ ተዘጋጅቶና ፀድቆ በቅርቡ ተግባራዊ እንደሚሆን አቶ ደምሰው ገልጸዋል፡፡

የአገር ውስጥ ቤተሙከራዎች ውሱን አቅም በምክንያት የማር ጥራትን ለማስመርመር ወደ ኡጋንዳና ጀርመን በመላክ በከፍተኛ ወጪ ይከናወን የነበረውን ሒደት አሁን ላይ ደረጃውን የጠበቁ ዘጠኝ ቤተሙከራዎችን በሀገር ውስጥ በማስገንባት ሒደቱን እዚሁ ለማስቀረት ጥረት እየተደረገ ነው፡፡

በማር ላይ እሴት በመጨመር የሚገኘውን የውጭ ምንዛሬ ለማሻሻል ሚንስቴሩ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሌሎች እንደ ቡና፣ ሰሊጥ ቆዳ፣ ሌጦና ሌሎች ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶች ሁሉ ጉልህ ሚና እንዲኖረው እየተሰራ ነው፡፡

የማር ምርት በተለይም በአውሮፓና አረብ አገሮች ተፈላጊ እንደሆነ ታውቋል፡፡

ከንብ ቀፎ የሚገኘውን ማር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ምርቶችንም መጠቀም ይቻላል፡፡ ቴከኖሎጂና በሙያው የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ምክንያት ግን ጠቀሜታው የተገደበ እንዲሆን አስገድዷል ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ በማር ምርታማነታቸው የኦሮሚያ፣ ደቡብ ሕዝቦች፣ የአማራና ትግራይ ክልሎች በቅደም ተከተል ተቀምጠዋል፡፡ የጋምቤላና ቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልሎችም ጥሩ ማር የማምረት አቅም አላቸው፡፡

ሚንስቴሩ በተያዘው በጀት ዓመት 80ሺህ ቶን ማር ለማምረት አቅዶ እየሰራ እንደሆነ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡