በትግራይ ክልል ከ1 ነጥብ 4 ሚሊየን በላይ ህዝብ የሚሳተፍበት የአፈርና ውሃ ጥበቃ ዘመቻ ስራ መጀመሩን የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ አስታወቀ ፡፡
የቢሮው የተፈጥሮ ሃብት ትግበራ አስተባባሪ አቶ አረፈ ኪሮስ ለዋልታ እንደገለጹት ፤ከዛሬ ጀምሮ በክልሉ በተፋሰሶች ላይ ለ20 ቀናት በሚካሄደው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ በየቀኑ 1 ሚሊየን 434 ሺህ 587 ህዝብ ይሳተፋል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
በክልሉ በ100 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል፡፡
በክልሉ በካርታ ተደግፎ በተለዩት 2ሺ 594 ተፋሰሶች በጥራት ለማካሄድ ልዩ ክተትል እንደሚደረግ ነው ያስረዱት ፡፡
በክልሉ ለዘመቻው የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶች በማዘጋጀት ከ84 ሺ 258 በላይ የልማት ቡድኖች መደራጀታቸውን አቶ አረፈ አስታውቀዋል፡፡
የአፈርና ጥበቃ ስራው ሰብል ጨርሶ ባልተሰበሰበባቸው ከሰሜን ምዕራብና ምዕራብ ዞኖች በስተቀር በሁሉም የክልሉ ገጠር ወረዳዎች እየተካሄደ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር አትንኩት መዝገቡ በደቡባዊ ዞን ዛሬ ስራውን በይፋ ማስጀመራቸውን ለመወቅ ተችሏል ።