ዓለም አቀፉ የፀሃይ ኃይል ምንጭ መሣሪያዎች አቅራቢ ኩባንያ የሆነው ሶላር ኪወስክ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ በኢትዮጵያ የተለያዩ የገጠር አካባቢዎች የፀሃይ ኃይል ምንጭ መሣሪያዎች በስፋት በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ገለጸ ።
የኩባንያው የአገር ውስጥ የማስፋፊያ ሥራ አስኪያጅ አቶ ሃኒባል ገብረመድህን ለዋልታ እንደገለጹት ኩባንያው የፀሃይ የኃይል ምንጭ መሣሪያዎችን በበቂ መጠን ለማቅረብ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች 23 ሱቆችን ከፍቷል ።
ኩባንያው በተለያዩ አካባቢዎች የሚያቀርባቸው የፀሃይ ኃይል ምንጭ መሣሪያዎች ለማባዣ ማሽኖች ፣ ለሞባይል ቻርጀር፣ ለቴሌቪዠንና ለሌሎች እቃዎች አገልግሎት መሥጠት የሚያስችሉ ናቸው ብለዋል ።
ኩባንያው ከአውሮፓ ህብረት ባገኘው ድጋፍ 40 ተጨማሪ የመሸጨያ ሱቆችን በመክፈት አገልግሎቱን ለማስፋት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገልጸዋል ።
ኩባንያው ከሚከፍታቸው 40 ከሚሆኑት አዳዲስ ሱቆች ውስጥ ሦስቱ ባለፈው ሳምንት በባሌ ኳሶ ማንሶ አካባቢ ሥራ መጀመራቸውን ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል ።
በአንዳንድ አካባቢዎች ኩባንያው ያቀረባቸው መሣሪያዎች የፀጉር ቤትና የዲኤስ ቲቪ ቴሌቭዥን ማሳያ አገልግሎትን ለመሥጠት ማስቻሉን የጠቀሱት ሥራ አስኪያጁ ኩባንያው በአፍሪካ በኬንያ ፣ ታንዛኒያ ፣ ማዳጋስካርና ረዋንዳ መሣሪያዎችን እያቀረበ ነው ብለዋል ።
ከሶላር ኪውስክ ሶሉሽንስ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያው የተገኘ መረጃ እንደሚያሳየው ኩባንያው እስካሁን ባቀረባቸው የፀሃይ ኃይል መሣሪያዎች 17ሺ ቤተሰቦች ተጠቃሚ መሆን የቻሉ ሲሆን በገጠር ጥቅም ላይ የማለውን ማሾን በመተካት ላይ ይገኛል ።
በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ ኃይል ባልተዳረሰባቸው የገጠር አካባቢዎች የፀሃይ ኃይል ምንጭን የሚጠቀም የህዝብ ቁጥር እያደገ መጥቷል ።
( ትርጉም : በሰለሞን ተስፋዬ )