ጠቅላይ ሚኒስትሩ ውጤታማ አመራር ለሕብረት ሥራ ማህበራት ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን አስገነዘቡ

ውጤታማ የሆነ አመራር የሕብረት ሥራ ማህበራት ስኬታማነት ወሳኝ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚ ኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ገለፁ፡፡

ጠቅላይ ሚንስትሩ የ4ኛውን ሀገር ዓቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም በዓልን ዛሬ በይፋ በከፈቱበት ወቅት  የሕብረት ሥራ ማህበራት ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሽግግርን ለማረጋገጥ ያላቸው ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በቀጣይ በውጤታማ አመራር ማገዝ የበለጠ ውጤት ለማስመዝገብ ዓይነተኛ ሚና እንዳለው ገልጸዋል፡፡

ማህበራቱ በአሰራር፣ በአደረጃጀትና በውጤታማነት ራሳቸውን በመፈተሽ ሀገሪቱ በኢኮኖሚያዊ ሽግግር በምታደርገው ሂደት ላይ ያላቸውን አስተዋጽኦ አጠናክረው ሊቀጥሉበት እንደሚገባ አስገንዝበዋል ፡፡

የሀገሪቱን የግብይት ሥርዓት በማዘመን የሸማቹንና የአምራቹን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ረገድም የሕብረት ሥራ ማህበራት ቀላል የማይባል አስተዋፅኦ እንዳላቸው አስረድተዋል ፡፡

ባሳለፍነው ዓመት ብቻ 12 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በሕብረት ሥራ ማህበራት ግብይት መካሄድ መቻሉ ዘርፉ በዕድገት ጎዳና ላይ ለመሆኑ አመላካች ነው ሲሉ አቶ ኃይለማርያም አክለው ገልጸዋል፡፡

የፌደራል ሕብረት ሥራ ኤጀንሲ ኃላፊ አቶ ኡስማን ሱሩሩ በበኩላቸው ዘርፉ በሀገሪቱ ላይ ያለውን አስተዋጽኦ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የሕብረት ሥራ ማህበራትን ቁጥር ከመጨመር ይልቅ ጥራት ላይ ያተኮረ ሥራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል ፡፡

መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ልዩ ትኩረትም በርካታ ሴቶችና ወጣቶች በ79 ሺህ መሰረታዊ የሕብረት ሥራ ማህበራት፣ 373 የሕብረት ሥራ ዩኒየንና 4 የሕብረት ሥራ ፌዴሬሽን ዘርፎች ተሰማርተው ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠላቸው እንደሆነ ኃላፊው አብራርተዋል፡፡

ማህበራቱና ዩኔዮኖቹ በሀገሪቱ 15 ነጥብ 4 ሚሊየን አባላትን የያዙ ሲሆን፤ ከ17 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ ካፒታል ማፍራታቸውን አስታውቀዋል ፡፡

ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየሙ “የሕብረት ሥራ ማህበራት ለዘላቂ ልማትና ስኬት!” በሚል መርህ በኤግዚቢሽን ማዕከል እየተከናወነ ነው፡፡

በአውሮፓ የኢኮኖሚ ኮሚሽን ትላንት የተጀመረው የ4ኛው አገር ዓቀፍ የሕብረት ሥራ ማህበራት ኤግዚቢሽን፣ ባዛርና ሲምፖዚየም እስከ የካቲት 8/2009 ዓመተ ምህረት ድረስ ለጎብኝዎች ክፍት እንደሆነ መገለጹን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል  ዘግቧል፡፡