የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባወጣው የበረራ የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በረራዎችን በማከናወን ከዓለም 11ኛ መውጣቱ ተገለጸ ።
ፍላይት ስታትስ የተባለ ዓለም አቀፍ የበረራ መረጃ ኩባንያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ 11ኛ ደረጃን የያዘው እኤአ በጥር በ2017 ካካሄዳቸው 8ሺ የሚሆኑት በረራዎች ውስጥ 81 በመቶ የሚሆኑት በተቀመጠላቸው የበረራ የጊዜ ሰሌዳ 15 ደቂቃ ውስጥ መንገደኞች በመዳረሻ ቦታቸው እንዲደርሱ ተደርጓል ።
አየር መንገዱ ለዋልታ በላከው መግለጫ እንደገለጸው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት በማከናወን በአፍሪካና በመካከለኛ ምስራቅ ከሚገኙ አየር መንገዶች ቀዳሚውን ሥፍራ አግኝቷል ።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማሪያም “በረራን በተያዘለት ፕሮግራም ማካሄድ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ክቡራን ደንበኞቻችን የሚያውቁት መሆኑንና በረራዎች በታለመላቸው ሰዓትና ደቂቃ ተጀምረው በተያለላቸው ሰዓትና ደቂቃ እንዲጠናቀቁ የአየር መንገዱ ሠራተኞች እየተጉ ነው ”ብለዋል ።
እንደ አቶ ተወልደ ገለጻ በረራዎችን በተያዘላቸው ፕሮግራም መሠረት ለማካሄድ እንቅፋት የሚሆኑ የተለያዩ ምክንያቶች ሊያጋጥሙ የሚችሉ ቢሆንም መንገደኞች ያለንም መንገላታት በረራዎችን ያለንምም መዘግየት እንዲከናወኑ ሁሌም ጥረቶቻችንን አጠናክረን እንቀጥላለን ።
አየር መንገዱ 12ሺ ሠራተኞችን በማቀናጀት ባስመዘገበው ምርጥ አፈጻጻም እኤአ በ2016 የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሽልማቶችን ማግኘቱን የሚናገሩት አቶ ተወልደ አየር መንገዱ በአፍሪካ አየር መንገዶች ማህበር የዓመቱ ምርጥ የአየር መንገድ በመሆን ለ5ኛ ጊዜ ከመሸለሙም በተጨማሪ አይር መንገዱ ምርጥ ሠራተኛን በመያዝም ጭምር በስካይ ትራክስ ተሸልሟል ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አገልግሎቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር የ15 ዓመት የስትራቴጂክ ዕቅድ በማውጣት በአፍሪካ ግዙፍ አየር መንገድ የመሆን ራዕዩን ለማሳካት እየሠራ ነው ።