ቢሮው በብዙሃን ትራንስፖርት ላይ አተኩሮ እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

የአዲስ አበባ ከተማ መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማሻሻል በብዙሃን ትራንስፖርት ላይ አተኮሮ እየሠራ መሆኑን ገለጸ ።

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ ለዋልታ እንደገለጹት በአዲስ አበባ ከተማ  በትራንስፖርት  ዘርፉ  የሚታየውን  ችግር  በዘላቂነት ለመፍታት ቢሮው በብዙሃን  ትራንስፖርት አገልግሎትና በትራፊክ  ማኔጅመንት ላይ ያተኮሩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በአዲስ አበባ ከተማ  ከህዝብ ቁጥር  ማደግ ጋር  በተያያዘ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ የመጣውን  የትራንስፖርት አገልግሎት ፍላጎት ለማስተናገድ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት የአንበሳ ፣የአልያንስና  የሸገር አውቶቢሶችን  ቁጥርን ለማሳደግ እየተሠራ ነው ብለዋል ።

በከተማዋ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠጡ አውቶቢሶችን ይበልጥ ለማሳደግ  850 የሚሆኑ አዳዲስ አውቶቢሶች አስተዳደሩ ግዥ እየተፈጸመ መሆኑን የጠቆሙት ዶክተር ሰለሞን 750 የሚሆኑት የአንበሳ አውቶቢሶች መሆናቸውንና 100 የሚሆኑት ደግሞ  በሸገር አማካኝነት ለተማሪዎች ብቻ አገልግሎት የሚሠጡ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

በከተማዋ እየተሠጠ ያለው የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን  ለማድረግ  የአውቶቢስ መቆሚያ ፣ የጥገና ሥራዎች  ፣የነዳጅ መቅጃና የስምሪት አገልገሎትን ለመሥጠት የሚያስችሉ ትልልቅ ዴፖዎችን በ1ነጥብ4 ቢሊዮን ብር በሸጎሌና በቃሊቲ እየተገነቡ መሆኑን ዶክተር ሰለሞን አስረድተዋል ።

በተጨማሪም ቢሮው የትራፊክ ፍሰት በሚበዛባቸው በፒያሳ ፣ መገናኛ አየር ጤናና ጦር ኃይሎች አካባቢ  በ200 ሚሊዮን ብር  ወጪ  የተርሚናል ግንባታ ሥራ መጀመሩን አያይዘው ገልጸዋል ።

በአዲስ አበባ ለፈጣን አውቶቢስ አገልግሎት ብቻ የሚውሉ እያንዳንዳቸው 15  ኪሎ ሜትር የሆኑ ስድስት የመንገድ መሥመሮች ግንባታዎች እንደሚካሄዱ የሚናገሩት ዶክተር ሰለሞን በከተማ የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅን የሚቀርፉ እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል ።

ቢሮው በሚቀጥሉት 15 ዓመታት ተግባራዊ የሚደረግ የአዲስ አበባ ከተማ  የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ስትራቴጂን ለአዲስ አበባ ምክር ቤት በማቅረብ በከተማዋ የተሻለ የመንገድ ደህንነትና የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ለማስቻል የበኩልን ጥረት እያረደረገ መሆኑ ታውቋል ።