በሀገሪቱ የተለያዩ ክልሎች ከ47 ነጥብ 5 ቢሊየን ብር በላይ በጀት የተለያዩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን እያካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን አስታወቀ ፡
የባለሰልጣኑ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ወንድሙ ዛሬ ለዋልታ እንደገለጹት ፤በተመደበው 47 ቢሊየን 530 ሚሊየን ብር በጀት ባለፈው መንፈቅ በጀት ዓመት በዋና መንገድ ስራዎች ፣በወቅታዊ ፣በመደበኛና በከባድ ጥገናዎች እየተካሄዱ ይገኛሉ ፡፡
በሀገሪቱ የተለያዩ አከባቢዎች መንደበኛ መንገዶች ጥገና 6ሺ 644 ኪሎሜትር ታቅዶ 5ሺ 858 ኪሎሜትር ስራ መከናወኑን አስታውቀዋል ፡፡
እንዲሁም በተለያዩ አከባቢዎች 268 ኪሎ ሜትር ከባድና ወቅታዊ መንገዶች ለመጠገን ታቅዶ 273 ኪሎ ሜትር መጠገኑን አቶ ሳምሶን አረጋግጠዋል፡፡
በአገናኝ መንገዶች ግንባታም 253 ኪሎሜትር ታቅዶ ከ210 ኪሎ ሜትር በላይ መከናወኑን ጠቁመዋል ፡፡
በዋና መንገዶች ደረጃ ማሻሻልም 107 ኪሎ ሜትር ታቅዶ ከ80 ኪሎ ሜትር በላይ መሰራቱን ገልጸዋል፡፡
በበጀት ዓመቱ ከላይ የተጠቀሱትን ስራዎች ማስፈጸሚያ የመደበኛ በጀትን ጨምሮ 47 ነጥብ 53 ቢሊየን ብር መመደቡን ጠቁመዋል ፡፡
ከዚሁም ውስጥ በአምስት ወራት ለካፒታል በጀት ከተመደበው 12 ቢሊየን 293 ሚሊየን 600 ሺህ ብር ውስጥ 6 ቢሊየን 633 ሚሊየን 700 ሺህ ብር ወጪ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል ፡፡
እንዲሁም ለመደበኛ በጀት ከተመደበው 53 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በሙሉ ወጨ መሆኑንም አቶ ሳምሶን ወንድሙ ገልጸዋል ፡፡