የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በ35 በመቶ ማደጉ ተገለጸ

ባለፉት  ስድስት  ወራት የኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በአማካኝ  በ35 በመቶ  ማደጉን  የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አስታወቀ ።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ መኮንን ሃይሉ ለዋልታ እንደገለጹት ኢትዮጵያ በዘንድሮ የበጀት ዓመት ባለፉት ስድስት ወራት 1ነጥብ 2 ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር የሚያወጣ የውጭ  ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ ችላለች ።

በግማሽ ዓመቱ የተመዘገበው የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ከመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የመጀመሪያ ዓመትና ከዓምናው የበጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጻር የሚያበረታታ ዕድገት አስመዝግቧል ።     

እንደ አቶ አቶ መኮንን ገለጻ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ዕድገቱ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች እየተቋቋሙ የሚገኙትና በብዙ ሚሊዮን ዶላር ወጪ እየፈሰሰባቸው የሚገኙት የኢንዱስትሪ ፓርኮች ትልቅ የሚባል አስተዋጽኦ አበርክተዋል ።   

ባለፉት ስድስት ወራት ከአውሮፓ፣ አሜሪካና ኢሲያ የመጡት ትልልቅ  ኩባንያዎች በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ለመሥራት  ገብተዋል ።   

ባለፉት ስድስት ወራት ሦስት የቻይና ኢንዱስትሪዎችና ሁለት የህንድ ኩባንያዎች በሐዋሳ የኢንዱስትሪ ፓርክ ሼዶችን በመውሰድ ሥራ ከጀመሩት የውጭ ኩባንያዎች መካከል የሚገኙ ሲሆኑ የውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንቱን በማሳደግ በኩል የጎላ ሚና ነበራቸው ።

በተለይም  ከሶስቱ የቻይና ኩባንያዎች  ጂያንግሱ ሰንሻይን ግሩፕ በአጠቃላይ 945 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በማፍሰስ ኢንቨስትመንቱን በኢትዮጵያ ለማስፋፋት ወስኗል ።    

 በተጨማሪም በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት፣ አንጻራዊ ሰላምና ርካሽ የሰው ሃይል  ለውጭ ቀጥታ ኢንቨሰትመንቱ  ፍሰት ዕድገቱ ሌላው አስተዋጽኦ ያደረጉ ምክንያቶች መሆናቸውን አቶ መኮንን አስረድተዋል ።

የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ማደጉ  በአገር ውስጥ ያለው ሥራ አጥ ዜጋ ወደ  ሥራ እንዲሰማራ እገዛ የሚያደርግ በመሆኑ   መንግሥት  ለኢንቨስትመንቱ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሠጥቶት እየሠራ እንደሆነ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።