ትግራይ ክልል ለ960 አዳዲሰ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች ፈቃድ ሰጠ

በተያዘው በጀት ዓመት የመጀመሪያ አጋማሽ ለ960 አዳዲስ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች ፈቃድ መስጠቱን የትግራይ ክልል ከተማ ልማት፣ ንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኢንቨስመንት ማስፋፋት የሥራ ሒደት ባለቤት አቶ ጎይቶም ገብረኪዳን ከዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በግማሽ ዓመቱ ለ1ሺህ 300 ባለሐብቶች የኢንቨስትመንት ፈቃድ ለመስጠት ታቅዶ 960ዎቹን ወይም 95 በመቶ ያህሉን ማሳካት ተችሏል፡፡

በገንዘብ ረገድም 10 ነጥብ 8 ቢሊየን ያህል የታቀደ ቢሆንም ባለሐብቶች በግዙግፍ የማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች በመሰማራታቸው 12 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ያህል ኢንቨስት ማድርግ ችለዋል፤ ይህ አሃዝ ከባለፈው በጀት ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በ4 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር ብልጫ እንዳለው አቶ ጎቶም አክለው ገልጸዋል፡፡

ማኑፋክቸሪንግ፣ ግብርና፣ ሆቴልና ቱሪዝም፣ የግንባታ ሥራዎችና የማህበራዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሐብቶች በኢንቨስትመንት ከተሰማሩባቸው ዘርፎች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡

ፈቃዱ ከተሰጣቸው የውጭ ባለሐብቶች ከአራት እንደማይበልጡና ቀሪዎቹ ሁሉም ኢትጵያውያን ባለሐብቶች ናቸው፡፡

እነዚህ አዳዲስ ባለሐብቶች ለ53ሺህ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ እድል መፍጠር እነደቻሉም ተገልጿል፡፡

አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችን በፍጥነት ወደ ሥራ መግባት ላይ መጓተት ተስተውሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታም ወደ ሥራ የገቡት ላይም ለኢንቨስትመንት የመረጡት ዘርፍ ላይ በቂ ጥናት ሳያደረጉ ሥራ መጀመር፣ የአመራር ድግፍ አናሳ መሆንና የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረትና መቆራረጥ ተጠቃሽ ችሮች ናቸው፡፡

ክልሉ የተጠቀሱትን ችግሮች በመቅረፍ በተለይ ክልሉ ለማኑፋክቸሪንግና አግሮ ፕሮሰሲንግ ዘርፎች ያለውን ምቹነት ተጠቅመው ባለሀብቶች ኢንቨሰት ቢያደርጉ ይበልጥ ውጤታማ የሚሆኑበትን ተግባራት እያከናወነ እንደሆነ አቶ ጎይቶም ጠቁመዋል፡፡

በተያዘው በጀት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የመቀሌ ኢንደስትሪ ፓርክ ወደ ሥራ ሲገባ በሚኖሩት 15 ሼዶች ባለሐብቶችን በመሳብ በክልሉ የበለጠ የኢንቨስትመንት ሥራ እንደሚከናወን ይጠበቃል፡፡

በትግራይ ክልል የኢንቨስትመንት ቢሮ ከተቋቋመበት ከ1985 ዓ.ም.  ጀምሮ ከ6ሺህ በላይ የኢንቨስትመንት ፕሮጄክቶች እንደተመዘገቡና ከ60 ቢሊየን ብር በላይ ኢንቨስት በማድረግ ከግማሽ ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፍጠር ችለዋል፡፡

በቅርቡ ሰሊጥና ሌሎች የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ፋብሪካ የሆነውን የሁመራ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ ግንባታ የመሰረተ ድንጋይ በጠቅላይ ሚንስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እንደተቀመጠ በማስታወስ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡