በቤኒሻንጉል ክልል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው

በቤኒሻንጉል ክልል ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ  ከ138ሺ በላይ  የክልሉ ነዋሪዎችን ያሳተፈ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ሥራዎች በ20 ወረዳዎች  እየተከናወኑ እንደሚገኙ የክልሉ መንግሥት አስታወቀ ።

የክልሉ የግብርና ቢሮ የተፈጥሮ ሃብት የሥራ ሂደት ባለቤት የሆኑት አቶ ደምስ መራ ለዋልታ እንደገለጹት በክልሉ ለወረዳ አመራሮችና  ለግብርና ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች ሥልጠና ከተሠጠ በኋላ ከአንድ ወር በላይ የሚቆይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የዘመቻ  ሥራዎች  በክልሉ እያንዳንዱ  ተጀምሯል ።             

የክልሉ መንግሥት ለአመራሩና ለግብርና ባለሙያዎች  አመራሩንና የግብርና ባለሙያውን በማቀናጀት በሠጠው ሥልጠና የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና እንክብካቤ ሥራዎች እንዴት በምን ደረጃ መከናወን  እንዳለባቸው ግንዛቤ ተሠጥቶበታል ።

አመራሩ  በክልሉ የዘመቻ ሥራ  የሚሳተፈውን ህብረተሰብ በማነቃነቅ ረገድ ተገቢውን  ሚና መጫወት እንዳለበት ትምህርት  በመውስድ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ያሉት አቶ ደምስ ባለሙያዎቹ  ሳይንሱ በሚያዘው መሠረት  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  በአግባቡ እንዲከናወነ እገዛ እያደረጉ ነው ብለዋል ።

በቤኒሻንጉል ክልል 378 ባለሙያዎች እና 128 አመራሮች ቀደም ብሎ ለስድስት ወራት የቆየ ሥልጠና በማግኘት ወደ ዘመቻ ሥራዎች  የገቡ ሲሆን  “ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ የዘመቻ ሥራ እስካሁን  ብዛት ያለው የክልሉ ነዋሪ እየተሳተፈ ነው ” ብለዋል አቶ ደምስ ።

ከዘመቻው  ሥራው  በተጨማሪ   ህብረተሰቡ  በእርከን ሥራዎችና ለክረምት ወራት የሚተከሉ  ችግኞችን የማዘጋጀትና  የመንከባከብ  ሥራዎችን እያካሄደ ነው ።

በዘንድሮ የበጀት ዓመት በመከናወን ላይ በሚገኘው  የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  የዘመቻ  ሥራ  ለመሸፈን ከታቀደው  42ሺ ሄክታር  መሬት  ውስጥ እስካሁን  ከ 8ሺ በላይ መሬት ላይ የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ  ሥራዎች ተካሄዷል ።