በአዲስ አበባ ከተማ የሚወገዱ ደረቅ ቆሻሻዎችን በመለየት መልሶ ጥቅም ላይ እንዲውሉ የሚያስችሉ ሁለት ማዕከላት እየተገነቡ መሆኑን የአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ፣ መልሶ መጠቀምና ማስወገድ ፕሮጀክት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።
የጽህፈት ቤቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አጥቁ ለገሰ ለዋልታ እንደገለጹት በአዲስ አበባ ከተማ በመጠን እየጨመረ የመጣውን የደረቅ ቆሻሻን በመጠቀም ለተለያዩ አገልግሎት እንዲውል ለማድረግ በ 92 ሚሊዮን ብር ወጪ በአቃቂና በቦሌ አራብሳ አካባቢዎች የማዕከላት ግንባታ እየተካሄደ ነው ።
ከአዲስ አበባ ከተማ ከተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የሚሰበሰቡ የደረቅ ቆሻሻዎች ረጲ የኃይል ማመንጫ ከመሄዳቸው በፊት በአቃቂና በቦሌ አራብሳ ማዕከላት እንዲለዩ እንደሚደረግ አቶ አጥቁ ተናግረዋል ።
የደረቅ ቆሻሻው አይነት ከተለዩ በኋላ ለረጲ የኃይል ማመንጫ ሊውሉ የሚችሉት ደረቅ ቆሻሻዎች ወደ ረጲ እንዲጓጓዙ ይደረጋል ያሉት አቶ አጥቁ የተቀሩት ደረቅ ቆሻሻዎች ኮምፖስት እንዲሆኑ ለማስቻል በማዕከላቱ የኮምፖስት ማስቀመጫ ሥፍራ ተዘጋጅቷል ብለዋል ።
በግንባታ ላይ በሚገኙት ሁለትማዕከላት ውስጥ በአዲስ አበባ የሚገኙ ሥራ አጥ ዜጎች በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሠማሩ የሚደረግ መሆኑን የሚገልጹት አቶ አጥቁ ከ200 በላይ የሚሆኑ የተደራጁ የኮምፖስት ዝግጅት ማህበራት በማዕከላቱ ለማሠራት ታቅዷል ።
በአዲስ አበባ የደረቅ ቆሻሻ አይነቶች ተለይተው ለተለያዩ ጥቅም እንዲውሉ ለማድረግ ከካምብሪጅ ዩኒቨርስቲ ፣ ከኢትዮጵያ መብራት ኃይልና ከደረቅ ቆሻሻና መልሶ መጠቀምና ማስወገድ ፕሮጀክት የተውጣጡ ባለሙያዎች በጋራ ተቀናጅተው እየሠሩ ይገኛሉ ።
በግንባታ ላይ የሚገኘው የረጲ ደረቅ ቆሻሻ የኃይል ማመንጫ ከሚሰበሰበው የደረቅ ቆሻሻ መጠን 90 በመቶው የሚሆነውን በመቀነስ በሰዓት 50 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም አለው ።
በአዲስ አበባ በየቀኑ ከ2ሺ 500 እስከ 3ሺ ቶን የሚደርስ ደረቅ ቆሻሻ እንደሚወገድ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።