ፌደሬሽኑ የወጣቶችን ተጠቃሚነት ለማጉላት እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ገለጸ

በአዲስ  አበባ  ከተማ  የሥራ አጥ ወጣቶችን በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሠማርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን  የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌደሬሽን አስታወቀ ።

የፌደሬሽኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ ወጣት አበባው ተስፋ ለዋልታ እንደገለጸው  በአዲስ አበባ  ከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች መንግሥት በመደበው የወጣቶች ተዘዋዋሪ ፈንድ  ተጠቅመው በተለያዩ የሥራ መስኮች በመሠማራት  ተጠቃሚነታቸውን  እንዲያሳድጉ ፌደሬሽኑ እየሠራ ይገኛል ። 

በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ወደ የተለያዩ አዳዲስ የሥራ ፈጠራ መስኮች እንዲሠማሩ ለማድረግ እስካሁን ድረስ ከተዘዋዋሪ ፈንዱ 400  ሚሊዮን ብር በጀት  መያዙን የጠቆመው ወጣት አበባው ለአስተዳዳራዊ ጉዳዮች ለሚውል ወጪ የአበባ ከተማ አስተዳደር  8 ሚሊዮን ብር መድቧል ብሏል ።

የተዘዋዋሪ ፈንዱ በምን መልኩ ጥቅም ላይ መዋል እንዳለበት ለወጣቶች ግንዛቤ ለመሥጠት እስካሁን ሁለት  የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን ፌደሬሽኑ ማዘጋጀቱን የሚናገረው ወጣት አበባው ወጣቶች ሥራን ሳይንቁ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች እንዲሰማሩ የቅስቀሳ ሥራን እያካሄደ ይገኛል ብለዋል ።

በአዲስ አበባ  ከተማ  በመጀመሪያ ዙር 19ሺ የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶችን ቤት ለቤት  በመቀስቀስ ፣ በመመልመል፣ በመለየትና በመመዝገብ  ፌደሬሽኑ ወደ ሥልጠና እንዲገቡ ማድረጉን ወጣት አበባው አስረድተዋል ።

እንደ ወጣት አበባው ገለጻ በመጀመሪያ ዙር የተመዘገቡት 19ሺ ወጣቶች ለሁለት ወር የሚቆይ ሥልጠና  በተለያዩ የቴክኒክና ሙያ ተቋማት እንዲከታተሉ ከተደረገ በኋላ በአሁኑ ወቅት በ16 ተቋማት የተግባር ተኮር ሥልጠና በመሳተፍ ላይ ናቸው ።  

በአጠቃላይ በአዲስ አበባ ከተማ  በዘንድሮ የበጀት ዓመት 156ሺ የሚሆኑ ሥራ አጥ ወጣቶች  በተለያዩ  መርሃ ግብሮች እንዲታቀፉ  በማድረግ የሥራ  ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ እየተሠራ መሆኑን  ከአዲስ አበባ  ከተማ አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል ።

የአዲስ አበባ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮማንድ ፖስት፣ የከተማዋ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ምክር ቤት ጋር በመቀናጀት በተለያዩ  ዘርፎች ለሚሠማሩ ወጣቶች ምን ያህል የብድር ገንዘብ እንደሚቀርብ የሚወስኝ የአሠራር መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን ወጣት አበባው ጠቁሟል ።

በመጨረሻም በአዲስ ከተማ የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች አሁን በተፈጠረው ምቹ አጋጣሚን በመጠቀም  ወደ  የተለያዩ የሥራ ዘርፎች ተሠማርተው እራሳቸውን ከመጥቀም ባለፈ  ለአገር ዕድገት እንዲተጉ ወጣት አበባው ጥሪ አቅርቧል ።