የኦሮሚያ ክልል በሁለተኛ ዙር 670ሺ ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ዝግጅቶችን እያጠናቀቀ መሆኑን የኦሮሚያ መስኖ ልማት ባለሥልጣን አስታወቀ ።
የባለሥልጣኑ ዋና ኃላፊ አቶ ሰይፈዲን መሓዲ ለዋልታ እንደገለጹት በኦሮሚያ ክልል በሁለተኛ ዙር በትናንሽ ፣ በመካከለኛና በትላልቅ የመስኖ ሥራዎች 670ሺ ሄክታር መሬት ለማልማት እየተዘጋጀ ነው ።
በክልሉ በመጀመሪያ ዙር 1ነጥብ3 ሚሊዮን ሄክታር መሬት በመስኖ ለማልማት ታቅዶ 86 በመቶ ወይም 977ሺ ሄክታር መሬት እንዲለማ ተደርጓል ያሉት አቶ ሰይፈዲን በመስኖ ሥራው 1ነጥብ 7 ሚሊዮን አርሶአደሮች ተሳትፈዋል ።
እንደ አቶ ሳይፈዲን ገለጻ በክልሉ የሚካሄደውን የመስኖ ልማት ስኬታማ ለማድረግ 1ሺ 620 ለሚሆኑ የግብርናና የልማት ባለሙያዎች የአሠልጣኞች ሥልጠና በዘንድሮ የበጀት ዓመት ተሠጥቷል ።
ለግብርናና የልማት ባለሙያዎች የተሠጠው ሥልጠና በመስኖ ልማት ቴክኖሎጂ፣ በውሃ ቁጠባ አሠራርና የግብይት አጠቃቀም ላይ የሚያተኩር መሆኑን የጠቆሙት አቶ ሰይፈዲን ሠልጣኞቹ በሥልጠና ያገኙትን ተሞክሮ በክልሉ የሚገኙ አርሶአደሮች እያስተላላፉ ይገኛሉ ብለዋል ።
በአሮሚያ ክልል በተለያዩ ደረጃዎች 2ነጥብ 45 ሚሊዮን የሚሆኑ አርሶአደሮችና ከፊል አርሶ አደሮች በየዓመቱ በመስኖ ሥራ እየተሳተፉ እንደሚገኙና የክልሉ መንግሥትም ለመስኖ ሥራዎች ማስፈጸሚያ 470 ሚሊዮን ብር መመደቡን አቶ ሰይፈዲን አያይዘው ገልጸዋል ።
በኦሮሚያ ክልል 533 የሚሆኑ የመስኖ አውታሮች የሚገኙ ሲሆን የመስኖ አውታሮችን ይበልጥ ለማስፋፋት የክልሉ መንግሥት ጥረት እያደረገ መሆኑን ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል ።