ክልሉ ከ244 ሺ በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠረ

በአማራ ክልል በቴክኒክና ሙያ ዘርፍ በተያዘዉ በጀት አመት ከ244 ሺ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የስራ እድል መፈጠሩን የቴክኒክና ሙያ ኢንተርኘራይዞች ልማት ቢሮ ገለጸ፡፡

የቢሮዉ ሃላፊ አቶ ላቀ አያሌዉ እንደገለጹት በተያዘው በጀት ዓመት በሀገርም ሆነ በክልል ደረጃ ለስራ ዕድል ፈጠራ ልዩ ትኩረት በመሰጠቱ በአማራ ክልል  በሚገኙ ሁሉም ዞንና ከተማ አስተዳደሮች የተከናወኑ ጥረቶች ከወዲሁ ዉጤት ማስመዝገብ ማስቻላቸዉን አመልክተዋል፡፡

ይሁን እንጂ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና ተያያዥ ተግባራት አኳያ ማለትም በስራ ፈላጊዎች ምዝገባ፣ በግንዛቤ ፈጠራ፣በስልጠና፣በገበያ ትስስር፣በማደራጀት እና በግብአት አቅርቦት ዙሪያ የሚታዩ ችግሮች መኖራቸውንም  ገልፀዋል፡፡  በአሰራር ላይ እያጋጠሙ ባሉ ችግሮች ዙሪያ ከተለያዩ ባለድርሻ  አካላት  የተለያዩ ጥያቄዎችንና አስተያየቶች  ተነስተው ውይይት  እንደተካሄደባቸዉም ጠቁመዋል፡፡
 

የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምንም እንኳ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ አመት ከወቅታዊው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ዝቅተኛ አፈፃፀም የነበረው ቢሆንም ከዚያ በኋላ ግን ወደ ዘጠኝ ሺ የሚጠጋ የስራ እድል መፍጠሩንና እና ለአፈፃፀሙም መሻሻል ዋነኛ ምክንያት በክልል ደረጃ የወጣው የወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠሪያ መመሪያ እንደሆነ ተመልክቷል፡፡
 

 እስካሁን ባለዉ አጠቃላይ ግምገማ  የታዩ ጠንካራ አፈፃፀሞችን ማጠናከር የሚገባ ሆኖ በእጥረት ከታዩት መካከል ዋና ዋናዎቹ ስራ አጦችን መመዝገብ፣ማደራጀት፣ግንዛቤ መስጠት እና የመሳሰሉትን እንደ ግብ አድርጎ መውሰድ፣በማህበረሰቡም ሆነ በስራ ፈላጊው መካከል ያሉ የግንዛቤ ክፍተቶችን እየለዩ አለማረም እና የስራ ዕድል ፈጠራው ቀጣይነት እንዲኖረው አድርጎ ያለመስራት ችግሮች በቀጣይ መስተካከል እንዳለባቸው አቅጣጫ  መሰጠቱንም አስገንዝበዋል፡፡
 

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የቴክኒክ እና ሙያ ኢንተርኘራይዞች ልማት ቢሮ የ2ዐዐ9 በጀት ዓመት የኢንተርኘራይዞች ምስረታ እና የስራ ዕድል ፈጠራ የ7 ወራት ዕቅድ አፈፃፀሙን የገመገመ ሲሆን በዚህም የአፈፃፀም ሂደት የታዩ ጥንካሬ እና እጥረቶች ቀርበዋል፡፡
 

በዚህ የግምገማ መድረክም  የክልሉን  ርዕሰ መስተዳድር  አቶ ገዱ አንዳርጋቸዉን ጨምሮ ሌሎች ከክልል ፣ ከዞንና ከከተማ አስተዳደሮች የተጋበዙ ባለድርሻ አካላትና  የቴክኒክና ሙያ ኢንተርኘራይዞች ልማት ቦርድ ሰብሳቢዎች፣ ቢሮ ኃላፊዎች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡