በትግራይ የእጣን ዛፍን ከጥፋት ለመጠበቅ ምርምር እየተደረገ ነው

 

በትግራይ ክልል የእጣን ዛፍ ሀፍትን ከጥፋት ለመታደግ በምርምር የተደገፈ ጥረት እየተደረገ መሆኑን  የክልሉ ግብርናና ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ገለጸ ።

በቢሮው የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ፣ እንክበካቤና ደን ልማት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ሀፍቱ ኪሮስ ለእንደገለጹት በክልሉ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ማዕከላዊ ዞኖች 384 ሺህ 200 ሄክታር   መሬት በእጣን ዛፍ የተሸፈነ ነበር፡፡

በሂደት በደረሰበት ጉዳት እየተመናመነ ሽፋኑ አሁን ላይ ወደ  267ሺህ 88 ሄክታር ዝቅ ብሏል።

የህገ ወጥ እርሻ መስፋፋት፣ ልቅ ግጦሽ፣ ደን ጭፍጨፋ፣  ቃጠሎና ስርዓት የሌለው የምርት አጠቃቀም ለተክሉ መመናመን በምክንያትነት ከተጠቀሱት ውስጥ ይገኙበታል ነው ያሉት ፡፡

በየዓመቱ ይገኝ የነበረው 50 ሺህ ኩንታል ምርት በማሽቆልቆሉ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢም እየቀነሰ መምጣቱን አመልክቷል፡፡

በትግራይ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የተፈጥሮ ሃብት ልማት ምርምር ምክትል አስተባባሪ አቶ ክንፈ መዝገበ በበኩላቸው በዘርና በግንድ ቆረጣ ዘዴ ዝርያዎችን ለማራባት የሚያስችል ምርምር እየተካሄደ  መሆኑን አስታውቀዋል።

የማይጸብሪና ሽሬ ግብርና ምርምር ማዕከላት ተክሉን በሰርቶ ማሳያዎች  ቆርጠው በመትከል ባደረጉት  የሙከራ ምርምር ተስፋ ሰጪ ውጤት መገኘቱንና ይህንኑ የማስፋፋት ስራ መጀመሩን ጠቅሰዋል ።

በተጓዳኝም  ከ20 እስከ 30 አባላት ያሏቸው  86 ማህበራት ተቋቁመው የእጣን ዛፍ ይዞታዎችን በመረከብ እንዲንከባከቡና ችግኝ እንዲተክሉ እየተደረገ መሆኑንም አስተባባሪው  ገልጸዋል።

የእጣን ዛፍ ሀብቱ ለመጪዎቹ ሶስት ዓመታት ከምርት ነፃ ሆኖ እንዲቆይ ይደረጋል፤ በይዞታው ላይም የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል።

የዕጣን ዛፍ  ለመድኃኒት፣ ለመስታወት፣ ለፕላስቲክ ቀለም፣ ለሽቶና ለተለያዩ ኬሚካሎች መስሪያ እንደሚውል ከትግራይ  የግብርና ምርቶች  ገበያ ፕሮሞሽን ኤጀንሲ  የተገኘው መረጃ ያመለክታል-(ኢዜአ) ።