ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ከ450ሺህ ብር በላይ የሚያወጡ ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽሕፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነት ዳይክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም ለዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት የግድቡ መሰረት የተጣለበትን ስድስተኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ እየተከናወኑ ባሉ የገቢ ማሰባሰቢዎች ግለሰቦች ለቶምቦላ ሎቶሪ ፕሮጄክት የሚውል 451ሺህ ብር የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለግሰዋል፡፡

የቶምቦላው ሎቶሪ በቅርቡ እንደሚጀምር ከጽሕፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

ባለሐብቶቹ ቀደም ሲል የቦንድ ግዢና የገንዘብ ስጦታ በማበርከትም የግድቡን ግንባታ ለማፋጠን የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ እንደቆዩም ታውቋል፡፡

የኢቴልኮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ባምቢስ ሱፐር ማርኬት፣ ኦልማርት ሱፐር ማርኬት፣ አምባሰል የግል ሥራዎች ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣ ቢቲ ሬድ ኢንተርናሽናል ትሬዲንግ፣ ሜትሮ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበርና ሴፍ ዌይ ሱፐር ማርኬት የቁሳቁስ ስጦታውን ያበረከቱ ደርጅቶች ናቸው፡፡

ማቀዝቀዣዎች፣ የቡና ማፍያዎች፣ የአቧራ መጽጃ ቁሳቁሶች፣ የልብስ ማጠቢያዎችና ምድጃዎች ከቁሳቁሶቹ መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ሌሎች ባለሐብቶች 579ሺህ500 የሚያወጡ የተለያዩ ቁሳቁሶችን ለማበርከት ቃል እንደገቡ አቶ ኃይሉ አክለው ገልጸዋል፡፡

ታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ከተበሰረበት ጊዜ ጀምሮ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ዋንጫ፣ ከ8100ኤ፣ የህዳሴ ሎተሪ፣ ከዳያስፖራው የገንዘብ ድጋፍ እና ከቦንድ ሽያጭ ሳምንት 9 ነጥብ6 ቢሊየን ብር መገኘቱን ይታወቃል፡፡ 

ቀደም ሲል 10 ሚሊየን ብር ከሚያስገኘው የሎቶሪ ሽያጭ ከ64 ነጥብ 7 ሚሊየን ብር በላይ ማሰባሰብ እንደተቻለም አቶ ኃይሉ ገልጸዋል፡፡

የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ የተቀመጠበት 6ኛ ዓመት በመጪው መጋቢት 24፣ 2009 ዓ.ም. “ታላቁ ሕዳሴ ግድባችን የሀገራችን ሕብር ዜማ የሕዳሴያችን ማማ” በሚል መሪ ቃል እንደሚከበር ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል ዘግቧል፡፡