የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ስኳር ፋብሪካ የሙከራ ምርት ጀመረ

በኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት እየተገነቡ ከሚገኙት አራት የስኳር ፋብሪካዎች ውስጥ የኩራዝ ቁጥር 2 ስኳር ፋብሪካ የሙከራ ምርት መጀመሩን ስኳር ኮርፖሬሽን አስታወቀ ፡፡

ከጥር 2009ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ የሙከራ ደረጃዎችን ያለፈው ፋብሪካው ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ከአራት ትናንት ደግሞ ስኳር ማምረቱን ነው ያመለከተው ፡፡

የስኳር ፋብሪካ ሥራ እንደጀመረ ወዲያውኑ በሙሉ አቅሙ ወደ መደበኛ የማምረት ተግባር ይገባል ተብሎ የማይጠበቅ ሲሆን ፤የሙከራ ሂደቱን ተከትሎ የተለያዩ የማስተካከያ ሥራዎች እየተሰሩ ከወራት በኋላ ወደ መደበኛ የማምረት ሥራ እንደሚሻገር አብራርቷል ፡፡

በቀን 12 ሺህ ቶን አገዳ የመፍጨት አቅም እንዲኖረው ተደርጎ የተገነባው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር 2 ፋብሪካ አሁን በቀን እስከ 6 ሺህ 500 ቶን አገዳ በመፍጨት ሥራ የጀመረ ሲሆን፣ ቀሪ የፕሮጀክቱ ሥራዎች በሂደት ሲጠናቀቁ ሙሉ አገዳ የመፍጨት አቅሙ ላይ ይደርሳል ብሏል ፡፡

ፋብሪካው ሙሉ የማምረት አቅሙ ላይ ሲደርስ በዓመት እስከ 2ነጥብ 5 ሚሊዮን ኩንታል ስኳርና 28 ሚሊዮን ሊትር የሚጠጋ ኤታኖል እንደሚያመርት ሲጠበቅ፣ ከሚያመነጨው 60 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል ውስጥም 20ውን ለራሱ ተጠቅሞ 40 ሜጋ ዋቱን ወደ ብሔራዊ ቋት ይልካል ተብሎ ይጠበቃል ነው ያለው ፡፡  

በሌላ በኩል ለኦሞ ኩራዝ ስኳር ልማት ፕሮጀክት የመስኖ መሰረተ ልማት አውታር ለመዘርጋት በደቡብ ውሃ ሥራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት፣ በኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ በቻይናው ጀይ ደብልዩ  ኤች ሲ (JWHC) ኩባንያ እና በራስ አቅም እስካሁን በተከናወኑ ሥራዎች 15 ሺህ ሄክታር ያህል መሬት ውሃ ገብ የተደረገ ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ በ13 ሺህ ሄክታር ላይ የሸንኮራ አገዳ ተተክሏል፡፡

ለአገዳ ተከላ ተጨማሪ የመሬት ዝግጅት ሥራም እየተከናወነ መሆኑን ጠቁሟል ፡፡

ዋልታ እንደዘገበው የቤቶች ግንባታን በተመለከተም በደቡብ ቤቶች ልማት ድርጅትና በራስ አቅም ሥራዎች እየተሰሩ ይገኛሉ፡፡

ከቻይና ዴቨሎፕመንት ባንክ በተገኘ 6ነጥብ 67 ቢሊዮን ብር ብድር ግንባታው በመካሄድ ላይ የሚገኘው የኦሞ ኩራዝ ቁጥር ሁለት ፋብሪካ ሥራ በይፋ የተጀመረው ሐምሌ 2006ዓ.ም በኮርፖሬሽኑና ግንባታውን በሚያካሂደው ኮምፕላንት በተባለ የቻይና ኩባንያ መካከል ስምምነት ከተደረሰበት ቀን ጀምሮ መሆኑን አስታውሷል ፡፡