በኢትዮጵያ በዓመትከ100ሺህ በላይ ሄክታር ደን ሰደድ እሳት ቃጠሎ እንደሚደርስበት የአከባቢ፣የደንና የአየር ንብረት ለውጥ ሚኒስቴር አስታወቀ ፡፡
የሚኒስቴሩ የደን አደጋ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አብረሃም ግዛው ዛሬ ለዋልታ እንደገለጹት ፤በሰው ሰራሽ ምክንያት ሰፊ የደን ሽፋን ባላቸው አከባቢዎች በተካሄደው የዳሰሳ ጥናት በዓመት ከ100ሺህ እስከ 150ሺህ ሄክታር ደን የእሳት ቃጠሎ ይደርስበታል ፡፡
የሚኒስቴሩ ዋንኛ ዓላማው ደንና ሰው አብሮ እንዲኖር ቢሆንም፤በደን አከባቢ የሚገኘው ነዋሪ ግን በደን ሃብቱ ላይ የተለያየ ችግር በማድረስ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡
ይህም በደን አከባቢ በንብ ማነብ ፣ለከብቶች አዲስ ሳር እንዲበቅል ፣ከሰል ለማክሰልና ለእርሻ ስራ በሚሉ ምክንያቶች ደኑ በእሳት እንደሚቃጠል አመልክተዋል፡፡
በዚህ ዓመትም ከ50ሺህ እስከ 60 ሺህ ሄክታር ደን ቃጠሎ እንደደረሰበት አቶ አብረሃም ገልጸዋል፡፡
በተለይም በደቡብ ኦሞ ዞን በጸማይ ወረዳና በዝቋላ አከባቢዎች የደን ሰደድ እሳት ቃጠሎ ቢደርስም በአከባቢው ህብረተሰብ ከአንድ እስከ ሶስት ቀናት በተደረገው የማጥፋት ርብርብ አደጋው ለመቆጣጠር መቻሉን አብራርተዋል ፡፡
በሁመራና በመተማ አከባቢዎች ግን በህብረተሰቡ ዘንድ የተሻለ ግንዛቤ እየተፈጠረ በመምጣቱ ዘንድሮ የሰደድ እሳት ቃጠሎ አለማጋጠሙን በአብነት ጠቅሰዋል ፡፡
ችግሩ ለመቅረፍም ሚኒስቴሩ ከክልል ባለድርሻ አካትና መገናኛ ብዙኋን ጋርበመተባበር ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል ፡፡
እንደዚሁም ከሚኒስቴሩ አንስቶ የደን ግብረ ኃይል የተቋቋመ ሲሆን ይህም በሁሉም አከባዎች አስከ ቀበሌ ድረስ ቨለመዘርጋት እየሰሩ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የደን ቃጠሎ የሚደርሰው ከየካቲት እስክ ሚያዝያ ወር ድረስ የሚደርስ በመሆኑ የመገናኛ ብዙኋን፣ የአመራር አካላትና ባለድርሻ አካላት ችግሩን ለመቅረፍ ዳሬክተሩ ጥሪ አስተላልፈዋል ፡፡